የአፍሪካ ሕብረት የብዝሃ ሕይወት ጥበቃ ስብሰባ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው

208

አዲስ አበባ ግንቦት 22/2015 (ኢዜአ)፦ የአፍሪካ ሕብረት የብዝሃ ሕይወት ጥበቃ ስብሰባ በአዲስ አበባ በመካሄድ ላይ ነው ።

በሕብረቱ ኮሚሽን የተዘጋጀው ስብሰባ የአፍሪካ፣ ካሪቢያንና ፓስፊክ የብዝሃ ህይወት አለም አቀፍ ስምምነት፣ የኮፕ-15 የተባበሩት መንግስታት የብዝሀ ሕይወት ስብሰባና 19ኛው በንግድ እንቅስቃሴ ምክንያት እንስሳትና እጽዋት ላይ ጉዳት ላለማድረስ የተደረገ ስምምነት ስብሰባ ውጤቶች ትግበራ ላይ ያተኮረ ነው።

የአፍሪካ ሕብረት የዘላቂ አካባቢ ጥበቃና ብሉ ኢኮኖሚ ዳይሬክተር ሀርሰን ኒያምቢ ብዝሃ ሕይወት በአፍሪካ ለቱሪዝም፣ ለመድኃኒት (ፋርማሲዩቲካል) ኢንዱስትሪ እና ንግድ ዘርፍ ያለው ፋይዳ ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።


 

ከብዝሃ ሕይወት የአካባቢን ማህበረሰብ በሚፈለገው መልኩ ተጠቃሚ አለመሆን፣ ሕገ-ወጥ ንግድ እና የአየር ንብረት ለውጥ ተጽእኖ በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮች ናቸው ብለዋል።
በመሆኑም በዓለም የብዝሃ ሕይወት ስብሰባ ውጤቶችንና ስምምነቶችን በቅንጅት መስራት እንደሚያስፈልግ አመልክተዋል።

በብዝሃ ሕይወት ላይ ትኩረት ያደረጉ መርሐ-ግብሮችን፣ የእንስሳትና እጽዋት ሕገ-ወጥ ንግድን  ለመከላከል የተዘጋጀውን ስትራቴጂና ቀጣይነት ያለው የደን አስተዳደር ማዕቀፍን መተግበር እንደሚያስፈልግ ነው ዳይሬክተሩ ያመለከቱት።


 

የአውሮፓ ሕብረት ተወካይ አውሬሊ ጎዴፍሮይ አፍሪካ የብዝሃ ሕይወትና አካባቢ ጥበቃ ድጋፉን እንደሚቀጥል ገልጸዋል።

ለአፍሪካ ቀጣይነት ያለው የብዝሃ ሕይወት ጥበቃ እና አጠቃቀም ዓለም አቀፍ ትብብርና ጥምረትና የገንዘብ ድጋፍ ወሳኝ እንደሆኑም አመልክተዋል።


 

የተባበሩት መንግስታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን የቴክኖሎጂ፣ አየር ንብረት ለውጥና የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ዳይሬክተር ጂን ፓል በበኩላቸው አገራት ቀጣይነት ያለው የብዝሃ ሕይወት እንዲኖር እያከናወኑ ያለውን ተግባር ያነሱ ሲሆን ኢትዮጵያ እያከናወነች ያለው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር ተጠቃሽ መሆኑን አንስተዋል።

በባለሙያዎች ደረጃ የተጀመረው ስብስባ እስከ ነገ ይቆያል። 

በሚኒስትሮች ደረጃ የሚደረገው ስብስባ ከነገ በስቲያ የሚጀመር ሲሆን በባለሙያዎች ደረጃ በቀረቡላቸው አጀንዳዎች ላይ ይመክራሉ ተብሎ ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም