በኢትዮጵያ የማህበራዊ ጥበቃ ስርዓትን ለማጠናከር የመንግሥትና የልማት አጋሮች ቅንጅታዊ አሰራርን ማጎልበት ይገባል- ዶክተር ማይክል ሳምሶን

157

አዲስ አበባ ግንቦት 22/2015 (ኢዜአ)  በኢትዮጵያ የማህበራዊ ጥበቃ ስርዓትን ለማጠናከር የመንግሥትና የልማት አጋሮች ቅንጅታዊ አሰራርን ማጎልበት እንደሚገባ  የዘርፉ ምሁር ዶክተር ማይክል ሳምሶን ተናገሩ።

ማህበራዊ ጥበቃ በመደበኛ እና መደበኛ ባልሆነ መንገድ ድህነትን፣ የዜጐችን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ስጋት፣ ተጋላጭነትን እና መገለልን ለመቀነስ የሚያስችል ርምጃ በመውሰድ ለሁሉም ተደራሽ የሆነ የተመጣጠነ ዕድገት በማረጋገጥ ላይ የሚያተኩር የማህበራዊ ፖሊሲ ማዕቀፍ አካል ነው።

በደቡብ አፍሪካ ኬፕታውን የሚገኘው የኢኮኖሚ ፖሊሲ ጥናት ተቋም ዳይሬክተር ና በአፍሪካ የማህበራዊ ጥበቃ ዙሪያ ምርምር የሚያደርጉት ዶክተር ማይክል ሳምሶን በጉዳዩ ላይ ከኢዜአ ጋር ቆይታ አድርገዋል።

እንደ ተመራማሪው ገለጻ የማህበራዊ ጥበቃ ስርዓትን ዕውን ለማድረግ ሁሉን አቀፍ የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ፖሊሲና ስትራቴጂን መተግበር ይጠይቃል።

ስርዓቱ ሁሉም ሰው በኢኮኖሚው ውስጥ ተሳታፊና ተጠቃሚ የሚሆንበት አውድ የማስፈን ጉዳይ በመሆኑ ለስኬቱ የመንግስታትና የአጋር አካላት ትብብር ወሳኝ ነው ብለዋል።

ከዚህ አንጻር የኢትዮጵያ መንግስት እና የልማት አጋሮች የማህበራዊ ጥበቃ ስርዓት ለመፍጠርና አካታች ዕድገትን ለማረጋገጥ እየሰሩ መሆኑን ጠቁመው፤ ይህ ይበልጥ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ገልጸዋል።

የአየር ንብረት ለውጥና ጦርነትን ጨምሮ በሰው ሰራሽና በተፈጥሯዊ አደጋዎች ሳቢያ በርካታ ዜጎች ማህበራዊ ጥበቃ እንደሚሹ በመጠቆም፣ መንግስትና ለጋሽ ድርጅቶች የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ ጀምሮ በርካታ ሥራ ይጠብቃቸዋል ነው ያሉት።

አረንጓዴ ኢኮኖሚ ለማህበራዊ ጥበቃ ስርዓት ሁነኛ ሚና እንዳለው የገለጹት ዶክተር ማይክል፤ በኢትዮጵያ የተጀመረው የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ልማት  ጤናማ አምራች ዜጋን ለመገንባትና የሀገር ዕድገትን ለማረጋገጥ እንደሚያስችል ገልጸዋል። 

የተባበሩት መንግሥታት ለጋሽ ድርጅቶችን፣ መንግስታዊና ሀገር በቀል የግል ተቋማትን ጨምሮ ከ140 በላይ ድርጅቶችን የሚያስተባብረው የኢትዮጵያ ካሽወርኪንግ ግሩፕ አስተባባሪ አቶ ኑርሁሴን ፈቂ፤ በ2016 የተመሰረተው ግሩፕ ተጠቃሚዎችን በመለየትና በጥሬ ገንዘብ ድጋፍ  ላይ ያተኮረ መሆኑን ይገልጻሉ።


 

ከፈረንጆቹ 2022 ጀምሮ ከ2 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ ዜጎች ከ44 ሚሊዮን ዶላር በላይ ጥሬ ገንዘብ ተደራሽ ማድረጉን ገልጸው፤ ዓላማውም በጥሬ ገንዘብ ድጋፍ ማህበራዊ ጥበቃን ማረጋገጥ ነው ብለዋል።

የለጋሽ ድርጅቶች ድጋፍ እያደገ መምጣቱን ገልጸው፤ አሁንም የማስተባበር ስራዎችን በማጎልበት ድጋፋቸውን እንዲያጠናክሩ እንደሚደረግ ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ የማህበራዊ ጥበቃ ፖሊሲ ሰነድ እንደሚያትተው ማህበራዊ ጥበቃ የልማታዊ ሴፍትኔትን፣ የሥራ ዕድልና የኑሮ ሁኔታን፣ የማህበራዊ መድን አገልግሎትን ማስፋፋት፣ መሠረታዊ አገልግሎት ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን እና ለጥቃትና በደል ተጋላጭ ለሆኑ የሕግ ጥበቃ እና ድጋፍ እንዲያገኙ ማስቻል ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም