የኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ የስፖርት ጆርናል ድረ-ገጽ በይፋ አስመረቀ

268

አዲስ አበባ ግንቦት 22/2015 (ኢዜአ)  የኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ በዘርፉ የሚካሄዱ የጥናትና ምርምር ስራዎችን ተደራሽ የሚያደርግ የስፖርት ጆርናል ድረ -ገጽ በይፋ አስመረቀ፡፡

አካዳሚው ድረ- ገጹን ይፋ ያደረገው ዛሬን ጨምሮ ለሁለት ቀናት የሚቆየው  8ተኛው ሀገር አቀፍ የስፖርት ምርምር ጉባኤ ላይ ነው።

የአካዳሚው የጥናትና ምርምር ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አመንሲሳ ከበደ፤ድረ-ገጹ የሀገሪቱ የስፖርት ተመራማሪዎች የምርምር ሥራቸውን ለማቅረብ እንዲችሉ እድሉን የሚያመቻች ነው ብለዋል።

በዋናነትም በዘርፉ የሚካሔዱ ጥናትና ምርምሮችን ለሁሉም አካላት ተደራሽ ለማድረግ ያግዛል ብለዋል። 

በድረ ገጹ ላይ ከሀገር ውስጥም ሆነ ሌሎች አካላት ተቀድተው ወይም ቀጥታ ተገልብጠው የመጡ ጥናቶችን ለመለየት የሚያስችል መተግበሪያ የያዘ መሆኑንም አስረድተዋል።

ይኸም በአብዛኛው የሚቀርቡ ጥናቶች መደርደሪያ ላይ ከመታየት ባለፈ ተደጋጋሚነት ያላቸው በመሆኑም ይሕንኑ ለማጣራትና አዳዲስ ምርምሮችን እንዲካሔዱ ለማድረግ የሚያበረታታ ነው ብለዋል።


 

ድረገጹ ሀገር በቀል ዕውቀቶች እንዲሰፉና ሳይንሳዊ ይዘት እንዲኖራቸው ከማድረግ ባለፈ የሀገሪቱን ስፖርት በጥናትና ምርምር ለማሳደግ ፋይዳው የጎላ እንደሆነም ገልፀዋል።

በተጨማሪም የኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ የጥናትና ምርምር ሥራዎችን ለመሥራት የሚጠቅሙ የስፖርት ምርምር ቤተ ሙኩራ አጠቃቀም የልኬት መመሪያ ማዘጋጀቱን ገልፀዋል።

በዚህም አካላዊ ልኬት፣ የልብ ሥርዓት ኡደት ልኬት፣ የደም ናሙና ልኬት፣ የብቃት ልኬት፣ የሥነ-ልቦና ልኬት፣ የብቃት አመልካች ልኬቶችና የብሔራዊ ቡድኖች አባላት የቅድመ ምርመራ አገልግሎቶችን እየሰጠ ነው ብለዋል።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም