በመዲናዋ ሕዝብና የጸጥታ መዋቅሩ ተቀናጅተው በመስራታቸው በሠላምና ጸጥታ ዙሪያ ለውጥ ተመዝግቧል-ወይዘሮ ሊዲያ ግርማ - ኢዜአ አማርኛ
በመዲናዋ ሕዝብና የጸጥታ መዋቅሩ ተቀናጅተው በመስራታቸው በሠላምና ጸጥታ ዙሪያ ለውጥ ተመዝግቧል-ወይዘሮ ሊዲያ ግርማ

አዲስ አበባ ግንቦት 22/2015 (ኢዜአ) ፦በአዲስ አበባ ከተማ በለፉት ዘጠኝ ወራት ሕዝብና የጸጥታ መዋቅሩ በመቀናጀት በሰሩት ስራ በሠላምና ጸጥታ ዙሪያ ለውጥ መመዝገቡን የአዲስ አበባ ከተማ ሠላምና ጸጥታ አስተዳደር ቢሮ ሃላፊ ወይዘሮ ሊዲያ ግርማ ገለጹ።
የአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ጸጥታ አስተዳደር ቢሮ እና የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ከማዕከል እስከ ቀጠና ከሚገኙ አመራሮችና ኦፊሰሮች ጋር የዘጠኝ ወራት የስራ አፈጻጸም ግምገማና በወቅታዊ የጸጥታ ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት እያደረጉ ነው።
የቢሮው ሃላፊ ወይዘሮ ሊዲያ ግርማ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ወንጀልን በመከላከል ረገድ ከፍተኛ ውጤት መመዝገቡን ገልጸዋል።
ሰላምና ደህንነት በዘላቂነት ማረጋገጥ የሚቻለው በሕዝብ ተሳትፎ መሆኑን በመረዳት ነዋሪዎች በስፋት እንዲሳተፉ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
ውጤቱ የተገኘው ህብረተሰቡን የሰላምና ደህንነት ባለቤት በማድረግ ተቀናጅቶ መስራት በመቻሉ ነው ብለዋል።
ከተማ አስተዳደሩ የከተማዋን ሠላምና ደህንነት ለማረጋገጥ በሁሉም የከተማ አካባቢዎች በርካታ የሰላም ሰራዊት ማደራጀት መቻሉን ተናግረዋል።
ይህም አካባቢውን ይጠብቃል አጠራጣሪ ነገሮችን ሲመለከት ለጸጥታ ሃይሉ ጥቆማ እንዲያደርግ ይደረጋል ብለዋል።
በዚህም ባለፉት ዘጠኝ ወራት በርካታ ሰዎች በወንጀል ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር እንዲውሉ ተደርጓል ብለዋል።
የሰላም ሰራዊቱ የሚመራበት ህግና ደንብ መዘጋጀቱን ጠቁመዋል።
በመሆኑም በመዲናዋ ለሠላምና ደህንነት ለማረጋገጥ የመንግስት፣ የሕዝቡና የጸጥታ አካላት ትብብር በተሻለ መጠናከሩን ተናግረዋል።
ጽንፈኝነት ሠላምንና ደህንነትን እንዳያውክ ለማድረግ ነዋሪው አጠራጣሪ ነገሮችን እንደሚከታተል ገልጸዋል።
በዚህ ሂደትም የታሰቡ እኩይ ሴራዎች መክሸፋቸውን ነው የተናገሩት።