ተደራራቢ ግብርን ለማስቀረት እና በታክስ ላይ የሚፈጸመውን ማጭበርበር ለመካለከል የቀረበው አዋጅ ጸደቀ

234

አዲስ አበባ ግንቦት 22/2015 (ኢዜአ) የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባካሄደው 23ኛ መደበኛ ስብሰባው ተደራራቢ ግብርን ለማስቀረት እና በታክስ ላይ የሚፈጸመውን ማጭበርበር ለመከላከል የቀረበውን አዋጅ አጽድቋል፡፡
 

በምክር ቤቱ የፕላን፣ በጀት እና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ደሳለኝ ወዳጄ ረቂቅ አዋጁን በተመለከተ ሪፖርትና የውሳኔ ሀሳብ አቅርበዋል፡፡

በኢትዮጵያ መንግስት እና በግራንድ ዱቺ ኦፍ ሉዘምበርግ መንግስት መካከል በገቢ ላይ የሚከፈለውን ግብር በሚመለከት ተደራራቢ ግብርን ለማስቀረት እና በታክስ ላይ የሚፈጸምን ማጭበርበር ለመከላከል የቀረበው ስምምነት የሁለትዮሽ ትብብርን ለማጠናከር የሚያስችል የህግ ማዕቀፍን የሚፈጥር ረቂቅ አዋጅ እንደሆነ አቶ ደሳለኝ ወዳጄ ገልጸዋል፡፡

የውጭ የግል ካፒታል ፍሰት እና ኢንቨስትመንት በኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ውስጥ ወሳኝ ድርሻ እንዳለው የገለጹት ሰብሳቢው፤ ስምምነቱ የሁለቱ ሀገራት ዜጎችን ብቻ ሳይሆን በሁለቱ ሀገሮች ነዋሪ የሆኑትንም ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማድረግ የሚስችል አዋጅ መሆኑን ለምክር ቤቱ አብራርተዋል፡፡ 

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ከገንዘብ ሚኒስቴር የህግ አማካሪ ጋር በተለያዩ መድረኮች በረቂቅ አዋጁ አስፈላጊነት ላይ በሰፊው እንደተወያዩም አክለው ገልጸዋል፡፡ 

የምክር ቤቱ አባላትም፤ ረቂቅ አዋጁ በታክስ ማጭበርበር የሚታዩ ግድፈቶችን ለማረም የሚያስችል እና የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት የሚያጠናክር አዋጅ ነው ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

ምክር ቤቱ በውሎው ረቂቅ አዋጁን አዋጅ ቁጥር 1295/2015 አድርጎ በሙሉ ድምጽ ማጽደቁን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በማህበራዊ ትስስር ገጹ አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም