በዞኑ ከ180 ሚሊዮን በላይ ችግኝ መትከል የሚያስችል ጉድጓድ መዘጋጀቱ ተገለጸ

271

አዳማ  ግንቦት 22/2015 (ኢዜአ) በምስራቅ ሸዋ ዞን በአረንጓዴ አሻራ መርሓ ግብር ከ180 ሚሊዮን በላይ ችግኝ መትከል የሚያስችል ጉድጓድ መዘጋጀቱን የዞኑ ግብርና ጽሕፈት ቤት ገለፀ።

በዞኑ አቃቂ ወረዳ ቢልብሎ ቀበሌ በመጪው ክረምት ለሚከናወነው አምስተኛው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የችግኝ መትከያ ጉድጓድ ዝግጅት ትናንት ተካሂዷል።

የዞኑ ግብርና ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ መስፍን ተሾመ በዚሁ ወቅት እንደገለፁት በዞኑ ከ260 ሚሊዮን በላይ የተለያዩ ችግኞች መትኪያ ጉድጓድ ለማዘጋጀት ታቅዶ እየተሰራ ነው ብለዋል።


 

በእስከ አሁኑ ሂደት 182 ሚሊዮን ጉድጓድ መዘጋጀቱን የገለፁት ሃላፊው ከእቅዱ  70 በመቶ ተሳክቷል ነው ያሉት።

በዞኑ 11 ወረዳዎች በሚገኙ 292 ተፋሰሶች ተለይተው ችግኝ መትከያ ጉድጓድ እየተዘጋጀ መሆኑን ጠቅሰው በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ዘርፈ ብዙ አገልግሎት የሚሰጡ የቆላ ዛፎች በስፋት ለመትከል ዝግጅት ተደርጓል ብለዋል።

በዚህም ቴምር፣ ቀርከሃ፣ ግሽጣ፣ ዜይቱንና ሌሎች ዛፎች እንዲሁም የእንስሳት መኖ እንደሚገኝበትም ገልጸዋል።

በችግኝ ጉድጓድ ዝግጅቱ አርሶ አደሮች፣ አርብቶ አደሮች፣ ሴቶችና ወጣቶች፣ ተማሪዎችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት እየተሳተፉ መሆኑን ገልጸዋል።

52 የመንግስት የችግኝ ጣቢያዎችን ጨምሮ በ1ሺህ 900 የግለሰቦችና ማህበራት የተለያዩ አገልግሎት የሚሰጡ ከ260 ሚሊዮን በላይ ችግኞች መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።

የምስራቅ ሸዋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አባቡ ዋቆ በበኩላቸው የችግኝ ዝግጅቱ ከሰውና እንስሳት ንኪኪ ነፃ የሆኑና ባለፈው በጋ የእርከን ማሰርና የተፋሰስ ልማት የሰራንባቸው ተራራዎችና የተራቆቱ ቦታዎች ላይ ነው ብለዋል።

ዘንድሮ የሚተከሉ ችግኞች እንደ ከዚህን በፊቱ የደን ልማት ብቻ ላይ ትኩረት ያደረጉ ሳይሆን ለምግብነትና ለአፈር ለምነት ጨምር ትልቅ ፋይዳ ያላቸውን  ችግኞች  በስፋት ለመትከል ዝግጅት እየተጠናቀቀ ነው ብለዋል።



 

''የጉድጓድ ዝግጅት እያከናወንበት ያለው የቢልብሎ ተራራ ከአምስት ዓመት በፊት የተራቆተና ምንም አይነት የዛፍና የሳር ዝርያ የሌለበት ነው'' ያሉት አቶ አባቡ ''በአረንጓዴ አሻራ ላይ በሰራ ነው ስራ ዛሬ የምታዩትን ውጤት አግኝተናል'' ነው ያሉት ።

በዚህም የተራቆቱ መሬቶች መልሶ አገግመዋል፣ ወንዞችና ዥረቶች መመለስ ከመቻላቸው ባለፈ ከቢልብሎ ተራራ ክረምቱን እየወረደ አርሶ አደሩ የሚቸገርበትን ጎርፍ ማስቀረት እንደተቻለም ገልጸዋል።

በአቃቂ ወረዳ የቢልብሎ ቀበሌ ነዋሪ ወጣት መኮንን ቱፋ በበኩሉ ቢልብሎ ተራራ ምንም አይነት ዛፍና ሳር ያልነበረበት ያገጠጠና የተራቆተ ቦታ ነበር ብለዋል።

ባለፉት ዓመታት በእርከን ማሰር፣ በተፋሰስ ልማትና በአረንጓዴ አሻራ በሰራነው ስራ ተራራው ተመልሶ በደን እየተሸፈነ ከመሆኑም ባለፈ የደረቁ ወንዞችና ዥረቶች ተመልሰው አሁን እየተጠቀሙበት መሆኑን አውስተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም