የቻይና የሕክምና ቡድን በዘውዲቱ መሸሻ ብርሃን የሕጻናት ማሳደጊያ ማዕከል ለሚገኙ ሕጻናት ነጻ የጤና ምርመራ እና ሕክምና አገልግሎት መስጠት ጀመረ - ኢዜአ አማርኛ
የቻይና የሕክምና ቡድን በዘውዲቱ መሸሻ ብርሃን የሕጻናት ማሳደጊያ ማዕከል ለሚገኙ ሕጻናት ነጻ የጤና ምርመራ እና ሕክምና አገልግሎት መስጠት ጀመረ
አዲስ አበባ ግንቦት 21/2015 (ኢዜአ)፡- የቻይና የሕክምና ቡድን በዘውዲቱ መሸሻ ብርሃን የሕጻናት ማሳደጊያ ማዕከል ለሚገኙ ሕጻናት ነጻ የጤና ምርመራ እና የሕክምና አገልግሎት መስጠት ጀምሯል።
የሕክምና ቡድኑ አገልግሎቱን የሚሰጠው በማዕከሉ ለሚገኙ 80 ሕጻናት ሲሆን፤ ከሕክምና በተጨማሪ የትምህርት እና የምግብ ቁሳቁስ ድጋፍ አድርጓል፡፡
የጤና ምርመራና ድጋፉ የተከናወነው የኢትዮጵያ ቀዳማዊት እመቤት ጽህፈት ቤት ከቻይና ቀዳማዊት እመቤት ጽህፈት ቤት ጋር በመተባበር መሆኑም ተገልጿል፡፡
በኢትዮጵያ የቻይና አምባሳደር ዣኦ ዢዩዋን የሕክምና ቡድኑ ለሕጻናቱ ሙሉ ምርመራ የሚያደርግ መሆኑን ገልጸው፤ ሕመም ለተገኘባቸውም ወዲያው የሕክምና አገልግሎት እንዲያገኙ ይደረጋል ብለዋል።
በአገር ውስጥ የማይቻል ሕመም የሚከሰት ከሆነም ወደ ውጭ አገር ሄደው ሕክምና እንደሚያገኙም ገልጸዋል።
በቻይና እና ኢትዮጵያ መካከል ያለው ዘርፈ ብዙ ትብብር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አምባሳደር ዣኦ አመልክተዋል።
የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጄ ዱጉማ በበኩላቸው፤ በዘውዲቱ መሸሻ ብርሃን የሕጻናት ማሳደጊያ ማዕከል አቅራቢያ የሚገኘው የጴጥሮስ ስቴሻላይዝድ ሆስፒታል ከሕክምና ቡድኑ ጋር በጋራ እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡
በቀጣይም በሌሎች ማዕከሎች መሰል አገልግሎቶች እንዲሰፉ ጥረት እንደሚደረግ ጠቅሰው፤የሁለቱ አገራት ቀዳማዊት እምቤት ጽህፈት ቤት ላደረጉት ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።
የዘውዲቱ መሸሻ ብርሃን የሕጻናት ማሳደጊያ ማዕከል ስራ አስኪያጅ ቀሲስ አበባየሁ በፍቃዱ የተደረገው ድጋፍ ለሕጻናቱ የሕክምና ጉዳይ እና ለማዕከሉ ችግር ምላሽ የሰጠ ነው ብለዋል።
የዘውዲቱ መሸሻ ብርሃን የሕጻናት ማሳደጊያ ማዕከል ከ30 ዓመታት በላይ ወላጅ አልባ ሕጻናትን ተቀብሎ በማሳደግ የሚታወቅ ግብረ ሰናይ ድርጅት ነው።