በቅዱስ ጴጥሮስ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የመለስተኛ ደም ባንክ አገልግሎት ተጀመረ - ኢዜአ አማርኛ
በቅዱስ ጴጥሮስ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የመለስተኛ ደም ባንክ አገልግሎት ተጀመረ
አዲስ አበባ ግንቦት 21/2015 (ኢዜአ)፡- የቅዱስ ጴጥሮስ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የመለስተኛ ደም ባንክ አገልግሎት መስጠት ጀምሯል፡፡
በማስጀመሪያ መርሐ- ግብሩ ላይ የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጄ ዱጉማ፣የኢትዮጵያ ደምና ቲሹ ባንክ አገልግሎት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ሀብታሙ ታዬን ጨምሮ ሌሎች የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።
መንግስት የደም ባንክ አቅርቦትና ተደራሽነትን በማስፋት ለእናቶች ሞት መንስኤ የሆነውን የደም እጦት ችግር ለመቅረፍ እየሰራ መሆኑን ዶክተር ደረጄ ገልጸዋል።
በዚህም በሁሉም ክልል የደም አገልግሎት እንዲስፋፋ መደረጉን ገልጸው በአሁኑ ወቅት ከ44 በላይ የደም ባንኮች በመላ ሀገሪቱ እንደሚገኙ አመልክተዋል።
የዛሬው መርሐ-ግብር ከ2010 ዓ.ም ጀምሮ በ70 ሆስፒታሎች የመለስተኛ ደም ባንክ አገልግሎት ለማቋቋም የተጀመረው ፕሮጀክት አካል መሆኑን ጠቁመዋል።
አገልግሎቱ በተለይ ከፍተኛ የወሊድ አገልግሎት ለሚሰጡ ሆስፒታሎች ተጨማሪ አቅም የሚፈጥር መሆኑን ነው ሚኒስትር ዴኤታው ያስረዱት።
መለስተኛ የደም ባንኮች ውጤታማ ሆነው እንዲቀጥሉ የኢትዮጵያ ደምና ቲሹ ባንክ አገልግሎትን ጨምሮ ባለድርሻ አካላት ክትትልና ድጋፍ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።
የኢትዮጵያ ደምና ቲሹ ባንክ አገልግሎት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ሀብታሙ ታዬ በበኩላቸው በደም መፍሰስ ምክንያት የሚከሰተውን የእናቶች ሞትን ለመቀነስ የመለስተኛ ደም ባንክ አገልግሎት ትልቅ ፋይዳ እንዳለው ገልጸዋል፡፡
በመሆኑም በሆስፒታሉ የመለስተኛ ደም ባንክ አገልግሎት መጀመሩ የእናቶች ሞትን ለመቀነስ በሚደረገው ጥረት የራሱ የሆነ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው አመልክተዋል።
የቅዱስ ጴጥሮስ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ዋና ስራ አስፈጻሚ ዶክተር መታሰቢያ መስፍን፤አገልግሎቱ በሆስፒታሉ መጀመሩ የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት እንደሚያግዝ ተናግረዋል፡፡
በተለይም የኢትዮጵያ ደምና ቲሹ ባንክ አገልግሎት ከደም ጋር በተገናኘ ያለበትን ጫና በማቃለል ረገድ ጠቀሜታ እንደሚኖረው ገልጸዋል።