ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ድንበር ዘለል ወንጀሎችን በመከላከል ረገድ ከጎረቤት አገራት ጋር  በቅንጅት እየሰራች ነው - ኮሚሽነር  ደመላሽ ገብረ ሚካኤል

አዲስ አበባ ግንቦት 21/2015 (ኢዜአ)፡-ኢትዮጵያ ሽብርተኝነትና ድንበር ዘለል ወንጀሎችን በመከላከል ረገድ  ከጎረቤት አገራት ጋር በቅንጅት እየሰራች መሆኑን  የወቅቱ የምስራቅ አፍሪካ የፖሊስ አዛዦች ህብረት ፕሬዝዳንትና የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል  ደመላሽ ገብረሚካኤል ገለጹ።

5ኛው  የምስራቅ አፍሪካ የፖሊስ አዛዦች ህብረት ልዩ ስብሰባ በአዲስ አበባ እየተካሔደ ይገኛል።

በስብሰባው ላይ የ14ቱ የቀጣናው አባል አገራት የፖሊስ አዛዦች፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአደገኛ እፅ እና ወንጀል ቢሮ እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።

የወቅቱ የምስራቅ አፍሪካ የፖሊስ አዛዦች ህብረት ፕሬዝዳንት እና የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ደመላሽ ገብረሚካኤል፤ በመድረኩ በቀጣናው ድንበር ዘለል የወንጀል ጉዳዮች ላይ ግምገማ ይደረጋል ብለዋል።

በተጨማሪም የምስራቅ አፍሪካ ቀጣና ህገወጥ የገንዘብ፣ የጦር መሳሪያ፣ የሰዎች ዝውውር እና የተደራጁ የሽብር ወንጀል ጉዳዮችን ለመከላከል በተዘጋጀ ሰነድ ላይ ምክክር ተደርጎ እንደሚጸደቅ ተናግረዋል።

የምስራቅ አፍሪካ ፖሊስ አዛዦች ህብረት የስፖርት ዝግጅትም የምክክሩ አካል መሆኑን ጠቅሰው፤ በዘንድሮ ዓመት የስፖርት ዝግጅቱን የሚያስተናግድ አገር ምርጫ ይደረጋል ብለዋል።

በቀጣናው አገራት የፖሊስ አዛዦች መካከል እያደገ የመጣው ትብብር ውጤታማ ድንበር ዘለል የወንጀል መከላከል ስራ እንዲፈጠር እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

መሰረታዊ ሰብዓዊ መብቶችን ባከበረ መልኩ በቀጣናው በወንጀል የሚጠረጠሩ ግለሰቦችን በተቀናጀ የመረጃ ቅብብሎሽ ህግ የማስከበር ተግባር እየተሰራ መሆኑም ጠቅሰዋል።

ኢትዮጵያም ህገወጥ የሰዎች ዝውውር፣ ሽብርተኝነት እና ድንበር ዘለል ወንጀሎችን በመካለከል ረገድ  ከጎረቤት አገራት ጋር በቅንጅት እየሰራች ነው ብለዋል።

ወንጀል በመፈጸም መነሻቸውን ከኢትዮጵያና ጎረቤት አገራት በማድረግ የሚንቀሳቀሱ ተጠርጣሪዎችን በተሻለ የመረጃ ቅብብሎሽ በቁጥጥር ስር በማዋል ለህግ እንዲቀርቡ እየተደረገ መሆኑንም ጠቁመዋል።

በኢንተርፖል የምስራቅ አፍሪካ ዋና ጸኃፊ ጌዲዮን ኪሚሉ፤ የፖሊስ አዛዦች በትብብር መስራት ወንጀለኞችን በቀላሉ ለፍርድ ለማቅረብ እንደሚያግዝ አብራርተዋል፡፡

የምስራቅ አፍሪካ የፖሊስ አዛዦች ህብረት የተሻሉ ተሞክሮዎችና የህግ አሰራሮችን በመውሰድ  የቀጣናውን ሰላምና ደህንነት ማስጠበቅ እንደሚጠበቅባቸውም ነው የጠቆሙት፡፡

በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአደገኛ እፅ እና ወንጀል ቢሮ የቀጣናው ተወካይ ኒይል ዋሊሽ፤ በወንጀል በመከላከል ስራ የዜጎችን ሰብዓዊ መብት ማስከበር የሚያስችል ሰነድ መዘጋጀቱን ገልጸዋል።

ሰነዱም ሽብርተኝነትን እና ድንበር ዘለል ወንጀሎችን በመከላከል ሂደት የዜጎችን መሰረታዊ ሰብዓዊ መብቶች ተጋላጭነት ለመቀነስ እንደሚያግዝ ተናግረዋል።

5ኛው መደበኛ ያልሆነ የምስራቅ አፍሪካ የፖሊስ አዛዦች ህብረት ስብሰባ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአደገኛ እፅ እና ወንጀል ቢሮ እና የጀርመን መንግስት ድጋፍ መዘጋጀቱም ተመላክቷል። 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም