ቀጥታ፡

በሰሜን ሸዋ ዞን በበጋ ወቅት የለማ ከ912 ሺህ ኩንታል በላይ ስንዴ መሰብሰቡን የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታወቀ

ደብረ ብርሃን ግንቦት21/2015(ኢዜአ)፡- በአማራ ከልል ሰሜን ሸዋ ዞን በበጋ መስኖ የለማ ከ912 ሺህ ኩንታል በላይ ስንዴ መሰብሰቡን የዞኑ ግብርና መምሪያ እስታወቀ ።

አርሶ አደሮች የመስኖ ልማቱ ከዚህ በፊት በግብርና ስራቸው ከሚያገኙት በላይ ገቢ በማስገኘት ተጠቃሚ እንደሚያደርጋቸው ገልጸዋል።

በመምሪያው የመስኖ ባለሙያ አቶ ድፌ ወንድማገኝ ለኢዜአ እንዳሉት  እንደ ሀገር በበጋ መስኖ ስንዴን በማልማት የዜጎችን የምግብ ዋስትና ከማረጋገጥ ባሻገር ስንዴ ለውጭ ገበያ ማቅረብ መጀመሯ ዘርፉ እንዲነቃቃ አግዟል።

በዞኑም በዘንድሮ የበጋ ወራት ከ188 ሺህ በላይ አርሶ አደሮች የተሳተፉበት የስንዴ ልማት መካሄዱን ገልጸዋል። 

በእዚህም ከ47 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በመስኖ ስንዴ የለማ ሲሆን፣ ከለማው መሬትም 1 ነጥብ 8 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ይሰበሰባል ተብሎ እንደሚጠበቅ ተናግረዋል።

እስካሁን ድረስም በ23 ሺህ 400 ሄክታር መሬት ላይ የለማ 912 ሺህ 400 ኩንታል ምርት መሰብሰቡን ባለሙያው አስታውቀዋል።

በበጋ ወራት የነበረው የበልግ ዝናብ ስርጭት በቆላማ አካባቢዎች በደረሱ ሰብል ላይ መጠነኛ ጉዳት ቢያደርስም፤ በደጋማ አካባቢዎች ግን ለሰብሉ እድገትና ፍሬያማነት መቹ ሁኔታ መፍጠሩን ገልጸዋል።

እስካሁን ያልተሰበሰበው የስንዴ ሰብል በዝናብ ጉዳት እንዳይደርስበት በቴክኖሎጂ በመታገዝ የምርት መሰብሰብ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን አስታውቀዋል። 

ልማቱ ከዚህ በፊት በተለየ ሁኔታ ተጠቃሚ እንደሚያደርጋቸው አርሶ አደሮቹ  እምነታቸውን ገልጸዋል።

በምንጃር ሸንኮራ ወረዳ ራን ቡቲ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ቁምላቸው ቦጋለ እንዳሉት፣ ግማሽ ሄክታር  መሬታቸውን በክላስተር በማልማት 27 ኩንታል ስንዴ ማግኘታቸውን ገልጸዋል።

በአካባቢው የገፀ ምድር እና የከርሰ ምድር ውሃ በስፋት ቢኖርም፤ በእውቀትና በአጠቃቀም ችግር ለልማት ሳይውል መቆየቱን የገለጹት ደግሞ በአንጎለላ ጠራ ወረዳ ጠገጎ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ታዱ እሸቴ ናቸው።

ከግብርና ባለሙያዎች በተሰጣቸው ትምህርትና ከመንግሥት በቀረበላቸው የምርጥ ዘርና የማዳበሪያ ድጋፍ በበጋ በስንዴ ካለሙት 1 ነጥብ 5 ሄክታር መሬት 50 ኩንታል ምርት እንደሚጠብቁ ገልጸዋል።

በዞኑ ባለፈው ዓመት በበጋ መስኖ በስንዴ ከለማው 2ሺህ 541 ሄክታር መሬት 101 ሺህ ኩንታል ምርት መገኘቱን ከግብርና መምሪያው የተገኘ መረጃ ያመለክታል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም