በሲዳማ ክልል ለአገራዊ ምክክሩ አጀንዳ መለየት የሚያስችል ስራ ተጀምሯል- የአገራዊ ምክክር ኮሚሽን

257

ሃዋሳ ግንቦት 21 /2015 (ኢዜአ)፡- በሲዳማ ክልል ለአገራዊ ምክክሩ አጀንዳ መለየት የሚያስችለውን ስራ መጀመሩን የአገራዊ ምክክር ኮሚሽን አስታወቀ።

የኮሚሽኑ ኮሚሽነሮች ተቋሙ እያከናወነ ያለውን ስራ አስመልክቶ ዛሬ በሃዋሳ ከተማ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።

ኮሚሽነር ዶክተር አምባዬ ኦጋቶ ፤ ኮሚሽኑ በያዘው እቅድ በሲዳማ ክልል በምክክር ሂደቱ የሚሳተፉ አካላትን በመምረጥ አጀንዳ መለየት የሚያስችለውን ስራ መጀመሩን ገልጸዋል።

በዚህም  ኮሚሽኑ ባዘጋጀው የተሳታፊዎች ልየታና የአጀንዳ ማሰባሰቢያ የአሰራር ስርዓት መሰረት  ተሳታፊዎች ከወረዳዎች፣ከከተማ አስተዳዳሮችና ከክልሉ እንደሚመረጡ ተናግረዋል።

ከወረዳ የሚመረጡ ተሳታፊዎች የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎችን የሚወክሉ ዘጠኝ የማህበረሰብ አደረጃጀቶች የተውጣጡ ሲሆኑ፣ ከየአደረጃጀቱ 50 ሰዎች ይለያሉ ብለዋል።

በክልል ደረጃም  ከሲቪክ ማህበራትንና ከሌሎችም የሚመለከታቸው ተቋማት የሚወከሉ እንደሚኖሩ ገልጸው፤  በክልሉ አራት ከተሞች ከማህበረሰቡ ጋር ውይይት እንደሚደረግም ነው ዶክተር አምባዬ ያስረዱት።

ሃዋሳ፣ይርጋለም፣በንሳና አለታ ወንዶ ከተወከሉ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር ለመወያየት የተመረጡ ከተሞች መሆናቸውን ተናግረዋል።

ተሳታፊዎች በሚለዩበት ወቅትም  ልዩ ትኩረት የሚያስፈልጋቸው ሴቶች፣ወጣቶችና አካል ጉዳተኞች በበቂ መጠን እንደሚወከሉና ተሳትፎ እንደሚኖራቸውም ኮሚሽነሩ አስረድተዋል።

የኮሚሽኑን ስራ የሚያግዙ ሰባት ተባባሪ አካላት በሂደቱ እንደሚሳተፉና በኮሚሽኑ አሰራር ላይ ስልጠና እንደሚወስዱ ጠቁመው፤ የተወከሉት አካላት በቂ ግንዛቤ ካገኙ በኋላ የአጀንዳ መረጣ ላይ በትኩረት እንደሚሰራ ተናግረዋል።

ኮሚሽኑ የሚያካሂደው ውይይት ከታችኛው የሕብረተሰብ ክፍል የሚጀምርና የሕዝብ ምክክር  እንደሚደረግበት ያመለከቱት ዶክተር አምባዬ፤ ስራውን ውጤታማ ለማድረግ መገናኛ ብዙሃን ተገቢውን መረጃ በመስጠት ህዝቡን ንቁ ተሳታፊ እንዲሆን ማድረግ አለባቸው ብለዋል።

ኮሚሽነር ዶክተር ዮናስ አዳዬ በበኩላቸው፤ አገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ብሔራዊ መግባባትን በመፍጠር አብሮነትን ለማጠናከርና ለሀገር ግንባታ ከፍተኛ ሚና እንዳለው አብራርተዋል።

ኮሚሽነር ዶክተር ተገኝወርቅ ጌጡ፤  በተወሰኑ የኢትዮጵያ ክፍሎች በምክክሩ ተሳታፊ አካላትን በመምረጥ አጀንዳ የመለየት ስራ መጀመሩን ጠቅሰው፣ መላው የሲዳማ ክልል ሕዝብም በዚህ ታሪካዊ ሂደት በንቃት እንዲሳተፍ መልዕክት አስተላልፈዋል።

ኮሚሽኑ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦችና በሐረሪ ክልሎች እንዲሁም በድሬዳዋ አስተዳደደር የሀገራዊ ምክክር ተሳታፊዎችን በመምረጥ አጀንዳ መለየት የሚያስችለውን ስራ መጀመሩም ተገልጿል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም