ቀጥታ፡

የግብርና ምርት አይነቶችን በማስፋትና የአመጋገብ ስርአትን በማሻሻል የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ የጥናትና ምርምር ስራዎች እየተከናወኑ ነው- ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት

አዲስ አበባ ግንቦት 21/2015 (ኢዜአ)፡-የግብርና ምርት አይነቶችን በማስፋትና የአመጋገብ ስርአትን በማሻሻል የምግብ ዋስትናን በዘላቂነት ለማረጋገጥ የሚያስችሉ የጥናትና ምርምር ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ገለጸ።

የኢትዮጵያ የግብርና አመራረት ከጥንት ጀምሮ በተወሰኑ ምርቶች ላይ የተንጠለጠለ በመሆኑ የበርካታ ዜጎችም የአመጋገብ ልምድም በጥቂት የምግቦች አይነቶች ላይ የተገደበ መሆኑ ይታወቃል።

የአገሪቱ የአየር ንብረት የተለያዩ የሰብል ምርቶችንና የአትክልትና ፍራፍሬ ተክሎችን ለማምረት ምቹ ቢሆንም የአመራረት ልምዱ ብዙም መሻሻል አለማሳየቱ ይነገራል።

እንደ አጠቃላይ በአፍሪካ የምግብ ዋስትናን በዘላቂነት ለማረጋገጥ የግብርና ምርት አማራጮችን ማስፋትና የአመጋገብ ስርአትን ማሻሻል እንደሚገባ የዘርፉ ምሁራን ይመክራሉ።

በተለይም ድርቅን መቋቋም የሚችሉ የግብርና ምርቶችን በስፋት በማምረትና የምግብ አማራጮችን በማስፋት የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ ይገባል ነው የሚሉት።

በኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የሥነ-ምግብ ተመራማሪው ተስፋዬ ዘሩ፤ የግብርና ምርቶችን ብዝሃነት ማስፋትና የአመጋገብ ባህልን ማሻሻል የምግብ ዋስትናን በዘላቂነት ለማረጋገጥ ወሳኝ መሆኑን ይናገራሉ።

ኢንስቲትዩቱ ሥርዓተ ምግብን ለማሻሻል የሚያስችሉ የተለያዩ የምርምር ስራዎች እያከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።

በአመጋገብ ሂደት የተለያዩ ምግቦችን የመጨመር ልምድ ማዳበር የተመጣጠነ ምግብ ከማግኘት ባለፈ ለጤንነት የላቀ ጠቀሜታ ያለው መሆኑን አስረድተዋል።

በመሆኑም በተለያዩ የአፍሪካ አገሮች የተለመዱና ከፍተኛ የምግብ ይዘት ያላቸውን የዕጽዋት፣ የአትክልትና የፍራፍሬ ምግቦችን በኢትዮጵያም በስፋት እንዲዘወተሩ ማድረግ ይገባል ብለዋል።

በተለይም ድርቅን የሚቋቋሙ፣ ጥሩ የምግብ ይዘት ያላቸውን ምርቶች በብዛትና በስፋት ማምረት ከተቻለ በምግብ ራስን ከመቻል ባለፈ የስራ እድል መፍጠርና ገቢም ማስገኘት የሚያስችል መሆኑን ተመራማሪው ገልጸዋል። 

የምርምር ተቋማት፣ ዩኒቨርሲቲዎችና አምራች ኢንዱስትሪዎች በዚህ ዙሪያ በትብብር ሊሰሩ ይገባልም ነው ያሉት።

በግብርና ሚኒስቴር የእንስሳት ዓሣ ልማት ዘርፍ አማካሪ ዶክተር ዮሐንስ ግርማ፤ ኢትዮጵያ እምቅ የመልማት አቅም ቢኖራትም እስካሁንም የምርት ብዝሃነቱ ዝቅተኛ መሆኑንና የአመጋገብ ልምዱም በአብዛኛው በጥቂት ምርቶች ላይ የተገደበ መሆኑን ይናገራሉ።


 

በአንድ አካባቢ ተመርተው ለምግብነት የሚውሉ በሌላ አካባቢ ለምግብነት የማይውሉ መኖራቸውን ጠቅሰው ይህንን ለማሻሻል በቀጣይ መስራት ይገባል ብለዋል።

በተለይም የምግብ አማራጮችን ማስፋትና የአመጋገብ ልምዶችን ማሻሻል የሁሉንም ተሳትፎና ጥረት ይጠይቃል ነው ያሉት።

በግብርና ምርትም ሆነ በአመጋገብ ልምድ የሌሎች አገሮችን ጠቃሚ ተሞክሮ በመጋራት በሂደት እንዲለመድ እየተሰራ መሆኑን ዶክተር ዮሐንስ ገልጸዋል።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም