ኮሚሽኑ በህዝቦች መካከል ልዩነት የሚፈጥሩ ጉዳዮችን በምክክር ለመፍታት ለሀገራዊ አንድነትና ሰላም እየሰራ ነው - ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ

219

ሚዛን አማን ግንቦት 21 ቀን 2015 (ኢዜአ)--ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ በህዝቦች መካከል ልዩነት የሚፈጥሩ ጉዳዮችን በምክክር ለመፍታት ለሀገራዊ አንድነትና ሰላም እየሰራ መሆኑን የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ ገለጹ።

ኮሚሽኑ ከደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ከተውጣጡ የማኅበረሰብ ክፍሎች ጋር በቦንጋ ከተማ እየተወያየ ነው።


 

በመድረኩ ላይ ንግግር ያደረጉት የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ እንዳሉት እንደ ሀገር መግባባትን ለመፍጠር እየተሰራ ነው ብለዋል።

በህዝቦች መካከል ልዩነት የሚፈጥሩ ጉዳዮችን በምክክር ነቅሶ በማውጣት ችግሮችን መፍታት በሚቻልበት መንገድ ላይ በማተኮር ሀገራዊ አንድነትና ሰላም ለማምጣት ኮሚሽኑ እየሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።

''ከምንም በላይ ሰላም ያስፈልግናል'' ያሉት ኮሚሽነሩ ሰላም ሲኖር የእርስ በርስ ግንኙነትና የባህል ልውውጥን ጨምሮ ሌሎች የልማት ትሩፋቶች እንደሚፈጠሩ አስገንዝበዋል።

እርስ በእርስ መግባባት በህብረተሰቡ ውስጥ መከባበርን እንደሚያመጣ ገልጸው በዚህ ረገድ በየአካባቢው የሚወከሉ የምክክሩ ተሳታፊዎች ትልቅ ሚና መጫወት እንዳለባቸው ተናግረዋል።

ባለፉት 1 ዓመት ከ4 ወራት ጊዜ ውስጥ በኮሚሽኑ የውይይት ጽንሰ ሀሳብ ላይ ከመነጋገር ጀምሮ የየአካባቢ ባህልና ነባራዊ ሁኔታ ጥናት እና ሌሎች የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች ሲሰሩ መቆየታቸውን ተናግረዋል።

በህዝቦች መካከል አለመግባባትን የሚያስከትሉ ጉዳዮችን ለመለየት ምክክሩ ከታችኛው መዋቅር ጀምሮ እንደሚካሄድ አመላክተዋል።

ኢትዮጵያ ሁሉም እኩል የሚወከልባትና እኩል ዜጎቿ ፍትሃዊ ተጠቃሚ የሚሆኑባት እንድትሆን የተጀመረው የውይይት መድረክ ትልቅ ሚና እንዳለው ገልጸዋል።

ለሁለት ቀናት በሚቆየው የውይይት መድረክ ላይ ኮሚሽኑ የአጀንዳ መሰብሰብ እና በምክክሩ ተሳታፊ የሚሆኑ የማኅበረሰብ አካላት አመራረጥ ላይ ተወያይቶ አቅጣጫ የሚያስቀምጥ ይሆናል ተብሏል።

በቦንጋ ከተማ እየተካሄደ ባለው በዚህ የውይይት መድረክ በክልሉ ውስጥ ከሚገኙ ሁሉም ወረዳዎችና የከተማ አስተዳደሮች የተውጣጡ የኅብረተሰብ ክፍሎች እየተሳተፉ ነው።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም