ቀጥታ፡

ኢዜአ መረጃን ተደራሽ ከማድረግ ባሻገር የኮሙኒኬሽን ባለሙያዎችን በሥልጠና በማብቃት ረገድ የበኩሉን ሚና እየተወጣ ይገኛል

አዲስ አበባ ግንቦት 21/2015(ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) መረጃን ተደራሽ ከማድረግ ባሻገር የኮሙኒኬሽን ባለሙያዎችን በሥልጠና በማብቃት ረገድ የበኩሉን ሚና እየተወጣ መሆኑን የተቋሙ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሰይፈ ደርቤ ተናገሩ፡፡

ኢዜአ በአዋጅ ከተሰጡት ተግባርና ኃላፊነቶች መካከል በሚዲያና ሕዝብ ግንኙነት ዘርፍ ሙያዊ ሥልጠናዎችን አደራጅቶ መስጠት ይገኝበታል።

በዚሁ መሰረት ከዚህ ቀደም ለተለያዩ ተቋማትየሕዝብ ግንኙነት ባለሙያዎች ሥልጠና የሰጠ ሲሆን፤ በዛሬው እለት ደግሞ ለገቢዎች ሚኒስቴር የሕዝብ ግንኙነት እና ኮሙኒኬሽን ባለሙያዎች ሥልጠና መስጠት ጀምሯል።

ሥልጠናው በሁለት ዙር ለተከታታይ አምስት ቀናት እንደሚሰጥ በሥልጠና ማስጀመሪያ መርሃ-ግብሩ ላይ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዋና ሥራ አስፈጻሚ  ሰይፈ ደርቤ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ ሥልጠናው በሁለቱ ተቋማት መካከል ልምድ የሚወሰድበት መሆኑን አንስተዋል።

ሁለቱ ተቋማት በአገር ውስጥ በርካታ ቅርንጫፍ ያላቸው እንደመሆኑ በየአካባቢው ካሉ ጽህፈት ቤቶች ጋር ያሉ ሥራዎችን ተደራሽ ለማድረግ ዕድል እንደሚፈጥር ጠቁመዋል።

በሥልጠናው በጽንሰ-ሀሳብ ከሚሰጠው ትምህርት ባሻገር በኢዜአ ካሉ የሥራ ክፍሎች ጋር ልምድ የሚቀስሙበት መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት መረጃን ተደራሽ ከማድረግ ባሻገር የኮሙኒኬሽን ባለሙያዎችን በሥልጠና በማብቃት ረገድ የበኩሉን ሚና እየተወጣ መሆኑንም ነው የተናገሩት፡፡

ኢዜአ በቀጣዮቹ ጊዜያት በሚዲያው ዘርፍ የተሻለ ተደራሽ ለመሆን የሚያስችሉትን ሥራ እያከናወነ መሆኑን የገለጹት ዋና ሥራ አስፈጻሚው ሰልጣኞች የአገልግሎት ጊዜያቸውን ሲያጠናቅቁ የተቋሙን ሥራዎች እንደሚመለከቱ ጠቁመዋል።

በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት የሥልጠና ምክርና ምርምር ማዕከል ኃላፊ አብዱራህማን ናስር በበኩላቸው፤ በስልጠና መርሃ ግብሩ በመልዕክት ቀረፃ፣ በኮሙኒኬሽን ስትራቴጂ እንዲሁም በንግግር ጽሑፍ አዘገጃጀት ላይ  ተግባር ተኮር ሥልጠናዎች እንደሚሰጡ ተናግረዋል።

በተጨማሪም ዜና አዘገጃጀት፣ በዜና ይዘት፣ በዜና ዕቅድ እና ትንታኔ ላይ ሥልጠና ይሰጣል ነው ያሉት፡፡

ሰልጣኞች በቆይታቸው ጊዜያቸውን በአግባቡ ተጠቅመው ማግኘት ያለባቸውን እውቀትና ክህሎት ይዘው መውጣት እንዳለባቸው አመላክተዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም