ቀጥታ፡

የአፍሪካ የሥራ ዕድል ፈጠራ ጉባኤ በኢትዮጵያ ሊካሄድ ነው  

አዲስ አበባ ግንቦት 21/2015 (ኢዜአ)፡- የአፍሪካ የሥራ ዕድል ፈጠራ ጉባኤ ከሰኔ 30 እስከ ሐምሌ 2/2015 ዓ.ም በኢትዮጵያ ይካሄዳል። 

የፎረሙ ቅድመ ስብሰባ ከዲፕሎማቲክ፣ ዓለም አቀፋ ተቋማት ተወካዮችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ተካሂዷል።

በመድረኩ ንግግር ያደረጉት የስራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ ንጉሱ ጥላሁን በአፍሪካ እያደገ የመጣውን አምራች የሰው ኃይል ለአህጉሪቷ ምጣኔ ሃብት እድገት እንደ እድል መጠቀም እንደሚገባ ጠቁመዋል።
 

ከዚህ አኳያ የኢትዮጵያ መንግሥት በወጣቶች የሥራ ዕድል ፈጠራ ላይ በትኩረት እየሰራ መሆኑን ነው የተናገሩት፡፡

ለዚህም ብሔራዊ የስራ ዕድል ፈጠራ ዕቅድ በማውጣት ተግባራዊ እየተደረገ ይገኛል ነው ያሉት፡፡

የአፍሪካ አገራት በወጣቶች የስራ እድል ላይ በትብብር መሥራት እንደሚጠበቅባቸውም ነው ሚኒስትር ድኤታው የተናገሩት፡፡
 

እቅዶችን በጋራ በማውጣትና በመተግበር በኩል በቀጣይ ሀምሌ ወር የሚካሄደው አህጉራዊ የስራ ዕድል ፈጠራ ጉባኤ ትልቅ ድርሻ እንዳለው ገልጸዋል።

ከሰኔ 30 እስከ ሐምሌ 2/2015 ዓ.ም ለሚካሄደው አህጉራዊ የሥራ ዕድል ፈጠራ ጉባኤ ስኬታማነት መንግሥት በቁርጠኝነት እንደሚሰራም አረጋግጠዋል።

በተባበሩት መንግስታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ተጠባባቂ ዋና ጸሀፊ አንቶኒ ፔድሮ በበኩላቸው በአፍሪካ በ2035 አምራች የሰው ሀይል ቁጥር 450 ሚሊየን እንደሚደርስ ተናግረዋል።

በመሆኑም አገራት በፍጥነት እያደገ ለመጣው የስራ ፈላጊዎች ቁጥር ስትራቴጅዎችን በመቅረጽና በአህጉሪቷ ያሉ የሥራ ዕድል ፈጠራ አማራጮችን መጠቀም ምላሽ መስጠት ይገባል ነው ያሉት።

የአፍሪካ አህጉራዊ ነጻ የንግድ ቀጠና አንዱ ትልቅ እድል መሆኑን በመጠቆም መንግስታት በቁርጠኝነት መስራት እንዳለባቸውም ነው ያስገነዘቡት፡፡

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም