የህዳሴው ግድብ የታችኛው ተፋሰስ አገራትን በጎርፍ አጥለቅልቆ በትነት የሚጠፋውን ውሃ በማስቀረት ሁሉንም ተጠቃሚ የሚያደርግ ፕሮጀክት ነው - ኢዜአ አማርኛ
የህዳሴው ግድብ የታችኛው ተፋሰስ አገራትን በጎርፍ አጥለቅልቆ በትነት የሚጠፋውን ውሃ በማስቀረት ሁሉንም ተጠቃሚ የሚያደርግ ፕሮጀክት ነው

አዲስ አበባ ግንቦት 21/2015(ኢዜአ)፡- ታላቁ የህዳሴ ግድብ የታችኛው ተፋሰስ አገራትን በጎርፍ አጥለቅልቆ በትነት የሚጠፋውን ውሃ በማስቀረት ሁሉንም ተጠቃሚ የሚያደርግ ፕሮጀክት መሆኑን የውኃ ኃብት አስተዳደር አማካሪው አቶ ፈቅአህመድ ነጋሽ ገለጹ፡፡
ግድቡ የናይልን ወንዝ የውሃ ፍሰት የማይቀንስ የተፋሰሱን ሀገራት ተጠቃሚ የሚያደርግ የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት መሆኑ በጥናት ጭምር ተረጋግጧል ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ ላይ ታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በመገንባት ለዘመናት የነበረው የዜጎቿ ቁጭት ምላሽ እንዲያገኝ በማድረግ አዲስ ታሪክ ጽፋለች፡፡
ይሁን እንጂ በቅኝ ግዛት ስምምነት መሰረት ውሃውን በብቸኝነት መጠቀም የሚፈልጉ የታችኛው ተፋሰስ ሀገራት የኢትዮጵያ ላይ በተለያየ መልኩ ጫና ለመፍጠር ሲሞክሩ ይስተዋላል፡፡
በተለይም ግብጽ "የናይልን ወንዝ በጋራ አልምተን በጋራ እንጠቀም" የሚለውን የኢትዮጵያን ፍትሃዊ ጥያቄ በቅንነት ከመቀበል ይልቅ አሁንም ወንዙን በብቸኝነት የመጠቀም ፍላጎቷን በግልጽ እያሳየች መሆኑንም አንስተዋል፡፡
የውኃ ኃብት አስተዳደር አማካሪው አቶ ፈቅአህመድ ነጋሽ ለኢዜአ እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ በታችኛው ተፋስስ ሀገራትን ላይ ጉልህ ተጽእኖ በማያደርስ መልኩ በናይል ወንዝ ላይ የመጠቀም ሉዓላዊ መብት አላት፡፡
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክትም የተፋሰሱን ሀገራት የውኃ ፍሰት የማይቀንስ ሁሉንም ተጠቃሚ የሚያደርግ የጋራ ኃብት መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ ላይ የምትገነባው የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት በመሆኑ ተፈጥሯዊውን የውኃ ፍሰት አይቀንሰውም ነው ያሉት አቶ ፈቅአህመድ፡፡
የአስዋን ግድብ የህዳሴውን ግድብ ከሶስት እጥፍ በላይ መሬት በውኃ የሚያጥለቀል ከመሆኑም በላይ በዓመት ከህዳሴ ግድብ አስር እጥፍ የሚበልጥና እስከ 17 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ የሚደርስ ውኃ በትነት እንደሚያጣ ተናግረዋል፡፡
በመሆኑም የታችኛው ተፋሰስ ሀገራት የታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የሚቃወሙት ጉዳት ስለሚያደርስባቸው ሳይሆን ኢትዮጵያ እንዳትለማ ካላቸው ፅኑ ፍላጎት በመነጨ ነው ብለዋል፡፡
የታላቁ ኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በአስዋን ግድብ ምክንያት በየሃምሳ ዓመቱ በግብጽ የሚከሰተውን የጎርፍ መጥለቅለቅ አደጋ የሚታደግ ፕሮጀክት መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
ከዚህም ባለፈ የናይል ወንዝ ሱዳንን በጎርፍ አጥለቅልቆ በትነት የሚጠፋውን ውኃ በማስቀረት ሁሉንም ተጠቃሚ የሚያደርግ ፕሮጀክት መሆኑ በጥናት የተረጋገጠ ነው ብለዋል፡፡
የአስዋን ግድብ አስር እጥፍ ውኃ በትነት እያጣ የሚያመነጨው ኃይል ከህዳሴው ግድብ ጋር ሲነፃፀር የጎላ ልዩነት እንዳለውም ጠቁመዋል፡፡