ኢትዮጵያን ወክለው በ7ኛው የሁዋዌ ዓለም አቀፍ የአይሲቲ ፍጻሜ ውድድር የተሳተፉ ተማሪዎች ሶስተኛ ደረጃን ይዘው አጠናቀቁ

347

አዲስ አበባ ግንቦት 21/2015(ኢዜአ)፦ በ7ኛው የሁዋዌ ዓለም አቀፍ የአይሲቲ ፍጻሜ ውድድር ኢትዮጵያን ወክለው የተሳተፉት ተማሪዎች ሶስተኛ ደረጃን ይዘው አጠናቀዋል።

ውድደሩ ከግንቦት 16 እስከ ግንቦት 20 ቀን 2015 በቻይና ሼንዘን ከተማ የተካሄደ ሲሆን በውድድሩ ከ36 አገሮች የተውጣጡ 146 ቡድኖች ተሳትፈዋል፡፡

ኢትዮጵያውያኑ ተማሪዎቹ እያንዳንዳቸው ሶስት አባላት ያላቸው ሶስት ቡድን በመሆን በፕራክቲካል ትራክ (ዳታኮም፣ሴኪዩሪቲ፣ገመድ አልባ የኮምፒዩተር ኔትወርክ ፣ ቢግ ዳታ፣ ስቶሬጅ፣ ሰው ሰራሽ አስተውሎት፣ ‘OpenEuler’ እና ‘OpenGauss’ የተሰኙ የመረጃ ቋትና የአሰራር ስርዓቶችን ያካትታል) ሁለት ቡድን እና አንድ ቡድን በኢኖቬሽን ትራክ ላይ ተሳትፈዋል።


 

በኢኖቬሽን ትራክ የተወዳደሩት ተማሪዎች “የግዕዝ ፊደላት ክላሲፋየር” የተሰኘ የፈጠራ ስራ መወዳደሪያ ይዘው መቅረባቸውን የትምህርት ሚኒስቴር በማህበራዊ ትስስር ገጹ ባወጣው መረጃ አመልክቷል።

የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ሳሙኤል ክፍሌ ውጤቱ ኢትዮጵያዊያን ተማሪዎች በሌሎችም ዘርፎች በአህጉራዊና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ መሆን እንደሚችሉ ያሳየ ነው ብለዋል።

የትምህርት ሚኒስቴር የትምህርትን ጥራት ለማረጋገጥ በተለይም በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ሆነው አገርን የሚያስጠሩ ዜጎችን ለማፍራት በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

የሁዋዌ ኢትዮጵያ ዋና ስራ አስፈጻሚ ሊዩ ጂፋን ተማሪዎቹ ባመጡት ውጤት መደሰታቸውን ገልጸው ድርጅቱ የአይሲቲ ዘርፉን ለማጠናከርና ተተኪዎችን ለማፍራት በቁርጠኝነት እንደሚሰራ አመልክተዋል።

ተማሪዎቹ በውጤታቸው መደሰታቸውንና ውድድሩ የሁዋዌን ዋና መስሪያ ቤት ከመጎብኘት አንስቶ ዓለም አቀፍ ተሞክሮ ያገኙበት መሆኑን ተናግረዋል።

ተማሪዎቹ በዓለም አቀፍ ውድድሩ ላይ የተሳተፉት የአገር ውስጥ ማጣሪያ ውድድሮችን በማለፍና በአገር አቀፍና አህጉራዊ ውድድሮች በማሸነፋቸው እንደሆነ ተገልጿል።

በውድድሩ ላይ የተሳተፉት ተማሪዎች ከጎንደር፣ ዋቸሞ፣ አዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ፣ አዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ እና አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲዎች የተገኙ መሆናቸውን የትምህርት ሚኒስቴር አስታውቋል።

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም