የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 26ኛ ሳምንት የመጨረሻ ጨዋታዎች ዛሬ ይካሄዳሉ

375

አዲስ አበባ ግንቦት 21/2015(ኢዜአ)፦በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 26ኛ ሳምንት መርሐ-ግብር የመጨረሻ ጨዋታዎች ዛሬ በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ይደረጋሉ።

በመርሐ-ግብሩ መሰረት ኢትዮጵያ መድን ከወልቂጤ ከተማ ከቀኑ ዘጠኝ ሰአት ላይ ይጫወታሉ።

በሊጉ የደረጃ ሰንጠረዥ ኢትዮጵያ መድን በ45 ነጥብ 3ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠ ሲሆን  ወልቂጤ ከተማ በ29 ነጥብ 14ኛ ደረጃን ይዞ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል።

ኢትዮጵያ መድን በፕሪሚየር ሊጉ ባደረጋቸው ያለፉት አምስት ተከታታይ የሊጉ ጨዋታዎች በሁለቱ አሸንፎ በአንዱ ተሸንፎ በሁለቱ አቻ ወጥቷል። 

በአንጻሩ ወልቂጤ ከተማ ካለፉት አምስት የሊግ ጨዋታዎች ማሸነፍ የቻለው አንድ ጊዜ ብቻ ነው። ሁለት ጊዜ ተሸንፎ በተመሳሳይ ሁለት ጊዜ አቻ ወጥቷል።

ሁለቱ ክለቦች በመጀመሪያ ዙር ያደረጉት ጨዋታ ኢትዮጵያ መድን 2 ለ 1 ማሸነፉ የሚታወስ ነው።

በ26ኛ ሳምንት የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ መርሐ-ግብር የመጨረሻው ጨዋታ በሀዲያ ሆሳዕና እና ኢትዮጵያ ቡና መካከል ከምሽቱ 12 ሰዓት ላይ ይደረጋል።

ሀዲያ ሆሳዕና በ36 ነጥብ 5ኛ ደረጃን የያዘ ሲሆን ኢትዮጵያ ቡና በ35 ነጥብ 7ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።

ሀዲያ ሆሳዕና ካለፉት አምስት ተከታታይ የሊግ ጨዋታዎች ማሸነፍ የቻለው አንድ ጊዜ ብቻ ነው። በአንዱ ተሸንፎ ሶስት ጊዜ አቻ ወጥቷል።

ተጋጣሚው ኢትዮጵያ ቡና በበኩሉ ባለፉት አምስት የሊጉ ጨዋታዎች ሁለት ጊዜ ሲያሸንፍ አንድ ጊዜ ተሸንፏል። ሁለት ጊዜ ነጥብ ተጋርቷል።

ሁለቱ ክለቦች በመጀመሪያው ዙር ያደረጉት ጨዋታ ሀዲያ ሆሳዕና 1 ለ 0 ማሸነፉ ይታወሳል።

ትናንት የሲዳማ ቡና እና ወላይታ ድቻ ጨዋታ እስከ እረፍት ያለምንም ግብ የተጠናቀቀ ቢሆንም በሃዋሳ በጣለው ከባድ ዝናብ ሜዳው ማጫወት እንደማይችል የጨዋታ አመራሮች በማረጋገጣቸው መቋረጡ ይታወቃል።


ከዛሬ ሁለቱ ጨዋታዎች ቀደም ብሎ ጨዋታው ከቆመበት ደቂቃ(ሁለተኛው አጋማሽ) በሃዋሳ ዩንቨርሲቲ ስታዲየም ከቀኑ 7 ሰዓት እንደሚደረግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አክሲዮን ማህበር አመልክቷል።


በሌላ በኩል ትናንት በተደረገ የ26ኛ ሳምንት ጨዋታ ድሬዳዋ ከተማ ፋሲል ከነማን 2 ለ 1  አሸንፏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም