በዋሽንግተን እና አካባቢው የሚኖሩ ዳያስፖራዎች በአዲስ አበባ የሚከናወኑ ሰው ተኮር ስራዎች እና ሜጋ ፕሮጀክቶችን የመደገፍ ፍላጎት እንዳላቸው ገለጹ - ኢዜአ አማርኛ
በዋሽንግተን እና አካባቢው የሚኖሩ ዳያስፖራዎች በአዲስ አበባ የሚከናወኑ ሰው ተኮር ስራዎች እና ሜጋ ፕሮጀክቶችን የመደገፍ ፍላጎት እንዳላቸው ገለጹ
አዲስ አበባ ግንቦት 21/2015 (ኢዜአ)፦ በዋሽንግተን እና አካባቢው የሚኖሩ ዳያስፖራዎች በአዲስ አበባ የሚከናወኑ ሰው ተኮር ስራዎች እና ሜጋ ፕሮጀክቶችን የመደገፍ ፍላጎት እንዳላቸው አስታወቁ።
የአዲስ አበባ ከንቲባ አዳነች አበቤ በዋሽንግተን እና አካባቢው ከሚገኙ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ጋር ፍሬያማ ውይይት ማድረጋቸውን በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መረጃ ገልጸዋል።
በውይይቱ ላይ ለዳያስፖራዎቹ አዲስ አበባ ስላሏት የኢንቨስትመንት አማራጮች መረጃ እንደተሰጣቸው ጠቁመዋል።
በውይይቱ በአዲስ አበባ ትላልቅ ሰው ተኮር ስራዎች እና ሜጋ ፕሮጀክቶች መሰራታቸውን የገለጹት ከንቲባዋ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በስራዎቹ ላይ ለመሳተፍ ያላቸውን ፍላጎት መግለጻቸውን አመልክተዋል።
ዳያስፖራዎቹ በገበታ ለትውልድ ፕሮጀክት የ200 ሺህ ዶላር ድጋፍ ለማድረግና ፕሮጀክቶቹም ተገንብተው እስኪጠናቀቁ በቀጣይነት ድጋፍ ለማድረግ ቃል መግባታቸውን ነው ከንቲባዋ የገለጹት።
በአሜሪካ ለነበረው ስኬታማ ቆይታ የኢትዮጵያ ኤምባሲ እና የዳያስፖራ አባላት ላደረጉት ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።