የጋሞ ዞን ሕዝብ ከመከላከያ ሰራዊት ጎን በመሆን ለአገር ልማት ይተጋል-የዞኑ መንግስት ተጠሪ - ኢዜአ አማርኛ
የጋሞ ዞን ሕዝብ ከመከላከያ ሰራዊት ጎን በመሆን ለአገር ልማት ይተጋል-የዞኑ መንግስት ተጠሪ
አርባ ምንጭ ግንቦት 20/2015 (ኢዜአ):- የጋሞ ዞን ሕዝብ በማንኛውም ሁኔታ ከመከላከያ ሰራዊት ጎን በመሆን ለአገር ልማት ይተጋል ሲሉ የዞኑ መንግስት ተጠሪ አቶ መልካሙ ቶንቼ ገለጹ።
የመከላከያ ሠራዊቱን የሚደግፍ ሰልፍ በጋሞ ዞን በአርባ ምንጭ ከተማ ተካሄዷል፡፡
በሰልፉ ስነ-ስርአት ላይ ንግግር ያደረጉት የዞኑ የመንግስት ተጠሪ አቶ መልካሙ ቶንቼ የሀገር መከላከያ ሠራዊት የሀገርን ደህንነት ከመጠበቅ ባለፈ በተለያዩ የልማት ሥራዎች እየተሳተፈ ይገኛል።
በዚህም አሻራውን እያኖረ የህዝብ ልጅ መሆኑን በተግባር እያረጋገጠ መሆኑን ገልጸው በህብረ ብሔራዊ አንድነት ስብጥር የተቋቋመው ይህ ተቋም የትኛውንም ፈተና የሚቋቋም ነው ብለዋል።
የዚህን ሰራዊት ስም የሚጎያድፉ አካላትን የዞኑ ሕዝብ በግልጽ በመቃወም ሰራዊቱን ይበልጥ እንዲደግፍና በልማት ስራው እንዲተጋ ጥሪ አቅርበዋል።
በመከላከያ ሰራዊት የጋሞ ዞን አካባቢ ላይዘን ጽህፈት ቤት ሃላፊ ኮሎኔል ገብሬ ግንባሬ በበኩላቸው ''ሀገራችን ኢትዮጵያ አንድነቷን በማጽናት ዳር ድንበሯንና ሉዓላዊነቷን ያስከበረች ሀገር ናት'' ብለዋል።
የተለያዩ ጽንፈኞች በሀገራዊና ህዝባዊ ተልዕኮ ላይ የሚገኘውን የሀገር መከላከያ ሠራዊት አንድነቱን ለመናድ በተለያየ መንገድ ሙከራ እያደረጉ ነው ብለዋል።
''ሕዝቡ በተወሰኑ ጽንፈኞች የሀገር መከላከያ ሠራዊት ላይ የሚነዙ የውሸት አሉባልታዎችን መቃወምና ትክክለኛ የሆነ እይታ መያዝ ያስፈልጋል'' ነው ያሉት።
''በጽንፈኞች እኩይ ተግባር መከላከያ ሠራዊቱ የሀገርና ህዝብን ተልዕኮ ከመፈጸም አያግደውም'' ያሉት ኮሌኔል ገብሬ ህዝቡ ከሠራዊቱ ጎን እንዲሰለፍ ጠይቀዋል፡፡
በሰልፉ ላይ ከታደሙት የአርባ ምንጭ ከተማ ነዋሪዎች መካከል ወይዘሮ መብራት መንግስቴ፣ ሁሌም የኢትዮጵያ ኩራት ከሆነው ጀግናው የሀገር መከላከያ ሠራዊት ጎን መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
ሰራዊቱ አሁን ካለበት ቁመና ይበልጥ እየደረጀ እንዲሄድ አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ ለማድረግ መዘጋጀታቸውንም ገልጸዋል፡፡
ከጋሞ ዞን ከተለያዩ መዋቅሮች የተወጣጡ ነዋሪዎች በአርባ ምንጭ ከተማ ባደረጉት ህዝባዊ ሰልፍ ላይ የተለያዩ መልእክቶችም ተላልፈዋል፡፡