ቀጥታ፡

የጅግጅጋና አካባቢዋ ነዋሪዎች  አንድነታቸውን የሚፈታተን የፅንፈኝነት እንቅስቃሴን እንደሚታገሉ አስታወቁ  

ጅግጂጋ ግንቦት 20/2015( ኢዜአ):-የጅግጅጋ ከተማና የአካባቢዋ  ነዋሪዎች ከሀገር መከላከያ ሠራዊት ጎን ሆነው አንድነታቸውን የሚፈታተን ማንኛውንም የፅንፈኝነት እንቅስቃሴ አንደሚታገሉ  አስታወቁ። 

የጅግጅጋ ከተማና አካባቢዋ  ነዋሪዎች "ጀግናው የሀገር መከላከያ ሠራዊታችን የኢትዮጵያዊያን ዋስትና በመሆኑ ሁሌም ከሠራዊታችን ጎን እንቆማለን” በሚል መሪ ሃሳብ በጅግጅጋ ስታዲዬም ዛሬ የድጋፍ ሰልፍ አካሂደዋል።

የሰልፉ ተሳታፊዎች ከሀገር መከላከያ ሠራዊት ጎን ሆነው አንድነታቸውን የሚፈታተን ማንኛውንም የፅንፈኝነት እንቅስቃሴ አንደሚታገሉ ገልጸዋል።

ለጀግናው የሀገር መከላከያ ሠራዊት እያደረጉት ያለውን ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉም አረጋግጠዋል።
 

ከሰልፈኞቹ መካከል አቶ መሀሙድ መሀመድ የሀገር መከላከያ ሰራዊት የነፃነታችን እና የአንድነታችን ተምሳሌት ነው ሲሉ  ለሰራዊቱ ያላቸውን አክብሮትና ፍቅር ገልጸዋል።  

ከሀገር መከላከያ ጎን ተሰልፈው አስፈላጊውን ሁሉ መስዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ መሆናቸውን ያረጋገጡት ደግሞ አቶ ሰይድ መሀመድ ናቸው። 

የጅግጅጋ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ኢንጂነር ሲያድ አብድ በዚሁ ጊዜ ባስተላለፉት መልዕክት የሀገር መከላከያ ሰራዊት የኢትዮጵያ ህዝቦች ሰራዊት በመሆኑ ምንጊዜም ከጎኑ እንቆማለን ብለዋል።

ከንቲባ አያይዘውም የጅግጅጋ ከተማና አካባቢዋ  ነዋሪዎች በራሳቸው ተነሳሽነት ለሀገር መከላከያ ሰራዊት ያላቸውን አጋርነት በድጋፍ ሰልፍ በመግለጻቸው አመስግነዋል።  
 

የፋፈን ዞን አስተዳደሪ አቶ አብዲሀኪን ሼኽ ሀሰን በበኩላቸው የሀገር መከላከያ ሰራዊት ውድ ህይወቱን ለህዝቦች ሰላምና አንድነት  እየከፈለ ነው ብለዋል።

በመሆኑም "ከመከላከያችን ጎን ሆነን አንድነታችን የሚፈታተን ማንኛውንም የፅንፈኝነት እንቅስቃሴ አጠብቅን እንቃወማለን " ሲሉ አረጋግጠዋል። 

በክልሉ የጎዴ፣ የፊልቱ፣ የዋርዴር፣ የደገህቡር፣ የቀብሪደሃር፣ የፊቅ ከተሞች ነዋሪዎች  ለሀገር መከላከያ ሰራዊት ያላቸውን ክብርና አጋርነት በሕዝባዊ ሰላማዊ ሰልፍ ገልጸዋል። 

ሰልፈኞቹ በሀገር መከላከያ ሠራዊት ላይ የሚፈፀመውን ስም ማጥፋት እኩይ ተግባር በፅኑ እንደሚቃወሙና ሠራዊቱን እንደሚደግፉ አረጋግጠዋል። 

“ጀግናው የሀገር መከላከያ ሠራዊት የኢትዮጵያዊያን ዋስትና በመሆኑ ሁሌም ከሠራዊቱ ጎን እንቆማለን” ሲሉም ያላቸውን ድጋፍ ገልጸዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም