ቀጥታ፡

በአዲስ አበባ የንግዱ ዘርፍ ማህበረሰብና ባለሃብቶች የግብርና ሳይንስ አውደ ርዕይን ጎበኙ

አዲስ አበባ ግንቦት 20/2015(ኢዜአ)፡-በአዲስ አበባ የንግዱ ዘርፍ ማህበረሰብና ባለሃብቶች በሳይንስ ሙዚየም የተዘጋጀውን የግብርና ሳይንስ አውደ ርዕይን ጎበኙ።

‹‹ከቤተ-ሙከራ ወደ አዝመራ›› በሚል መሪ ሃሳብ በሳይንስ ሙዚየም የተዘጋጀው የግብርና ሳይንስ ኢግዚቢሽን ሚያዝያ 29 ቀን 2015 ዓ.ም በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ተመርቆ ለተመልካቾች ክፍት መደረጉ ይታወቃል።

በአውደ ርዕዩ ላይ በግብርናው ዘርፍ የተገኙ የተለያዩ ስኬቶችን የሚያሳዩ የምርምርና የፈጠራ ስራዎች፣ ዲጂታላይዜሽንና የግብርና ፋይናንስ ላይ ያተኮሩ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች ለዕይታ ቀርበዋል።

በዚህም የተለያዩ ተቋማት ሰራተኞች፣ አርሶ አደሮች፣ በተለያዩ የክፍል ደረጃ ያሉ ተማሪዎች፣ የዩኒቨርሲቲ መምህራንና ተማሪዎች፣ የመንግስት ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች፣ የሃይማኖት አባቶችና ሌሎችም አውደ ርእዩን ጎብኝተዋል።

በዛሬው እለትም በአዲስ አበባ የንግዱ ዘርፍ ማህበረሰብና ባለሃብቶች በሳይንስ ሙዚየም በመገኘት ጎብኝተዋል።

ከጉብኝቱ ታዳሚዎች መካከል የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት ፕሬዘዳንት ኢንጀነር መላኩ አዘዘው፤ በጉብኘቱ በርካታ አስደናቂ የቴክኖሎጂና የፈጠራ ውጤቶችን ተመልክተናል ብለዋል።

በግብርናው ዘርፍ የተገኙ ስኬቶችና የፈጠራ ስራዎች በቀጣይ ለዘርፉ እድገት ትልቅ ተስፋ የሰነቁ በመሆናቸው ጥሩ ጅምር አለ ሲሉ አድናቆታቸውን ገልጸዋል።

በመሆኑም ለግብርናው ዘርፍ ቀጣይነት ያለው እድገት በተለይም ባለሃብቱና የንግዱ ማህበረሰብ የድርሻውን ለማበርከት መዘጋጀት አለበት ብለዋል።

በጉብኝቱ የተሳተፉ ነጋዴዎችና ባለሃብቶች በአውደ ርእዩ በተመለከቷቸው የቴክኖሎጂ ውጤቶች መደነቃቸውን ገልጸዋል።

የግብርና ሳይንስ የፈጠራ ስራዎቹ በቀጣይ ተግባራዊነታቸው እየተስፋፉ ሲሄድ ከዘርፉ ልማት ባሻገር ለአገር እድገትና ለዜጎች ኑሮ ማሻሻል አይነተኛ ሚና የኖራቸዋል ብለዋል።

በመሆኑም ለግብርናው እድገት፣ ዘመናዊ አሰራርና ምርታማነት ለሚከናወኑ ተግባራት የድርሻቸውን ለማበርከት ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።

የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ሶፊያ ካሳ፤ የኢትዮጵያ ግብርና ያለፈበትን ሂደትና አሁን የደረሰበት ደረጃ የንግዱ ማህበረሰብና ባለሃብቶች ማየታቸው የላቀ ፋይዳ አለው ብለዋል።

የኢትዮጵያ ግብርናን ለማሳደግ በሚደረገው ጥረት የባለሃብቱና የንግዱ ማህበረሰብ ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰው በቀጣይ ዘርፉን እንዲያግዙ ጠይቀዋል።

በቀጣይ በተመረጡ የግብርና መስኮች ለመሠማራት ለሚሹ ባለሃብቶች የአውደ ርዕዩ ጉብኝት መልካም አጋጣሚ መሆኑንም ዶክተር ሶፊያ ገልጸዋል፡፡

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም