የጓንዦ ከተማን ከኢትዮጵያ ከተሞች ጋር ማጎዳኘት ያስፈልጋል--ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን - ኢዜአ አማርኛ
የጓንዦ ከተማን ከኢትዮጵያ ከተሞች ጋር ማጎዳኘት ያስፈልጋል--ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን
አዲስ አበባ ግንቦት 20/2015 (ኢዜአ)፦የጓንዦ ከተማን ከኢትዮጵያ ከተሞች ጋር ማጎዳኘት መንግስት ፍላጎት ያለው መሆኑን የኢፊዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ገልጸዋል።
በቻይና ጉብኝት እያደረጉ ያሉት አቶ ደመቀ የጓንዦ ከተማ ከንቲባ ጉዎ ዮንጋንግ ባደረጉላቸው የእንኳን ደህና መጡ ግብዣ ላይ እንደተናገሩት የህዝብ ለህዝብ ትስስሩ የበለጠ እንዲጠናከር በጓንዦና በኢትዮጵያ ከተሞች መካከል ጉድኝት መፍጠር ጠቃሚ ነው ብለዋል።
የጓንዦ ከተማ 16 ሚሊዮን ነዋሪ ያላት ስትሆን የቻይና የቢዝነስ መናኸሪያ የሆነው ጓንዶንግ ግዛት ዋና ከተማ ናት።
የከተማው ከንቲባ የኢትዮጵያ የወጪ ምርቶች መዳረሻቸውን በጓንዦ እንዲያደርጉ ለኢትዮጵያ አምራቾች ጥሪ አቅርበዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ጓንዦ በመብረር ሁለቱን አገሮች ብቻ ሳይሆን ቻይናና አፍሪካን እንዳስተሳሰረ ጠቅሰው፤ በተለይም የኮቪድ ወረርሽኝ ወቅት በጓንዦ የሚያደርገውን በረራ ባለማቋረጡ አመስግነዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጓንዦ ቆይታቸው የኤሌክትሮኒክስ፣ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂና ከሃይል ማመንጫ ጋር የተያያዙ ኩባንያዎችን በመጎብኘት በኢትዮጵያ እንዲሰማሩ ጋብዘዋል፡፡