ቀጥታ፡

መከላከያ ሰራዊቱ የአገር ባለ ውለታ ነው - የሀረማያ ከተማ ከንቲባ

ሃረማያ ግንቦት 20/2015(ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት በአገረ መንግስት ግንባታ ታሪካዊ ሚና የተጫወተ የአገር ባለ ውለታ መሆኑን የሀረማያ ከተማ ከንቲባ ዶክተር ኢፍራህ ወዚር ገለፁ፡፡

በምስራቅ ሃረርጌ ዞን ሃረማያ ከተማ የአገር መከላከያ ሰራዊቱን የሚደግፍ ህዝባዊ ሰልፍ ተካሂዷል ፡፡

በድጋፍ ሰልፉ ላይ ከዞኑ የተለያዩ ወረዳዎች የተውጣጡ ነዋሪዎች የተሳተፉ ሲሆን፤ ''እሱ ሞቶ እኛን ያኖረንን ሰራዊት ማጠልሸት ይቁም''፣ ''መከላከያችን አንድነታችንን ይገነባል" ፣ "ጽንፈኞች ያፍራሉ'' የሚሉ  መልዕክቶች ተላልፈዋል።

''የኢትዮጵያዊነታችን አርማ የሆነውን መከላከያ ሰራዊት በመተንኮስ የስልጣን ፍላጎትን ማሳካት አይቻልም'' "ፅንፈኞች ከሰራዊቱ ላይ እጃቸውን ያንሱ" የሚሉና ሌሎች የተለያዩ መፈክሮችም ተሰምተዋል፡፡

በድጋፍ ሰልፉ ላይ መልእክት ያስተላለፉት የከተማው ከንቲባ ዶክተር ኢፍራህ ወዚር እንዳሉት  የአገር መከላከያ ሰራዊቱ በኢትዮጵያ አገር መንግስት ግንባታ ታሪካዊ ሚና የተጫወተ የአገር ባለውለታ ሰራዊት ነው፡፡


 

መከላከያ ሰራዊቱ የውስጥና ውጭ ጠላቶች በአገር ላይ የደቀኑትን አደጋ ለመቀልበስ የህይወት መስዋትነት በመክፈል  የኢትዮጵያን ሉአላዊነት ያስከበረ የአገር አለኝታ መሆኑንም አክለዋል።

ሰራዊቱ ሁሉንም ኢትዮጵያን ለአንድ አላማ በአንድ ጥላ ስር ያሰባሰበ  የህብረ ብሄራዊነት መገለጫ መሆኑንም ክንቲባዋ ገልፀዋል፡፡

ሰራዊቱ  በየትኛውም የአገሪቱ ክፍል በሚያጋጥሙ ሰው ሰራሽ እና የተፈጥሮ አደጋዎች ቀድሞ ምላሽ በመስጠትና ከመደበኛ ተልእኮው ባሻገር  ለአቅመ ደካሞች መኖሪያ ቤት በመገንባት፣ ለአርሶ አደሩ ሰብል በመሰብሰብ በልማት ስራም የተሳተፈ የልማት አርበኛ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ሰራዊቱ ህዛባዊነትን የተላበሰ መሆኑን በመጠቆም የመከላከያ ሰራዊትን  በተመለከተ ፅንፈኞች እያሰራጩት የሚገኘውን የስም ማጥፋት ዘመቻ እንደሚቃወሙ ገልፀዋል፡፡  

የምስራቅ እዝ 302ኛ ኮር አዛዥ ብርጋዴር ጀኔራል መለሰ መንግስቴ በበኩላቸው ህዝቡ በሰራዊቱ ላይ የተከፈተውን የስም ማጥፋት ዘመቻ በመቃወም ያካሄደው የድጋፍ ሰልፍ ህዝቡ ለሰራዊቱ ያለውን አጋርነት ይበልጥ ያሳየበት ነው ብለዋል፡፡

ሰራዊቱ በተለያዩ ጊዜያት ተልእኮ ተሰጥቶት በሚፈፅምበት ጊዜ ህዝቡ አስፈላጊውን ድጋፍ ማድረግ የተለመደ ተግባር መሆኑንም አክለዋል፡፡

አሁንም ቢሆን ሰራዊቱ ከወገንተኝነት በጠራ መንገድ ለማንኛውም ፓርቲ ሳይወግን በራሱ ህግና ስርአት የሚመራ ተቋም መሆኑን መገንዘብ እንደሚገባ ገልፀዋል፡፡

ይሁን እንጂ የተለያዩ የውስጥ እና የውጭ ፅንፈኞች ሰራዊቱን ወገንተኛ አድርገው ስሙን እያጠለሹ ቢሆንም ሰራዊቱ  የኢትዮጵያ ህዝብን ድጋፍ ይዞ የሚራመድ በመሆኑ ለፅንፈኞች አሉባልታ መቼም ቢሆን የማይንበረከክ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም