ቀጥታ፡

መከላከያ ሰራዊታችን ለኢትዮጵያ አንድነት መስዋእት በመሆን አገርን ያጸና ነው -በኦሮሚያ የተለያዩ ከተሞች የሰልፉ ተሳታፊዎች

ጭሮ/ሮቤ/መቱ/ግምቢ/ነገሌ  ግንቦት 20/2015 (ኢዜአ)፦ መከላከያ ሰራዊታችን ለኢትዮጵያ አንድነት መስዋእት በመሆን አገርን ያጸና ነው ሲሉ የኦሮሚያ ክልል ዞኖች የድጋፍ ሰልፉ ተሳታዎች ገለጹ፡፡

በኦሮሚያ ክልል ባሉት ዞኖች፣ የከተማ አስተዳደሮችና ወረዳዎች ነዋሪዎች የአገር መከላከያ ሠራዊት ክብርን የሚገልጽና ድጋፍን የሚያጠናክር ሕዝባዊ  የድጋፍ ሰልፍ  አካሄደዋል።

በምዕራብ ሀረርጌ ዞን አስተዳዳሪ ወይዘሮ ኤክራም ጠሃ በጭሮ ከተማ በተደረገው ሰልፍ ላይ ባደረጉት ንግግር መከላከያ ሰራዊታችን መደበኛ ተልዕኮውን ከመወጣት ባሻገር በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ችግሮች ቀድሞ ህዝባችን ጎን በመቆም አለኝታነቱን ያሳየን የምንጊዜም ጀግናችን  ነው፡፡
 

ህዝቡ ፅንፈኝነትን በመቃወም ለመከላከያ ሰራዊቱ የሚደረገውን ድጋፍ በማስቀጠል የሀገሪቷን ሁለንተናዊ ብልፅግና  እንዲያረጋግጥም  ጠይቀዋል፡፡

የሰልፉ ተሳታፊ የተለያዩ የምዕራብ ሀረርጌ ዞን ነዋሪዎችም ለመከላከያ ሰራዊታችን የምናደርገው ድጋፍ ይቀጥላል መከላከያችን በህይወት የመኖር ህልውናችን ነው ሲሉም ገልጸዋል፡፡

የዞኑ አስተዳዳሪ ለመከላከያ ሰራዊቱ ያላቸውን ክብር ለመግለፅም ጋሻና ጦር እንዲሁም የሀረር ሰንጋ በስጦታ አበርክተዋል፡፡

የባሌ ዞን ነዋሪዎችም ለሀገር መከላከያ ሠራዊት ያላቸውን ክብር የሚገልጽና ድጋፋቸውን የሚያጠናክር መፈክር አንግበው መውጣታቸው ተመላክቷል። 

በሮቤ ከተማ በተደረገው ሰልፍ ላይ የከተማ ከንቲባ አቶ ንጋቱ ሞቱማ እንዳሉት፣ የሀገር መከላከያ ሠራዊት የሀገር ሉዓላዊነት ምልክት በመሆኑ የሠራዊቱን ስም ማጠልሸት መቆም አለበት።
 

የባሌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብዱልሀኪም አልይ በበኩላቸው፣ የዞኑ ነዋሪዎች ባላቸው  አቅም ሁሉ ከመከላከያ ሰራዊት ጎን ሆኖ ድጋፉን በበለጠ አጠናክሮ እንዲቀጥል አሳስበዋል።

በመርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት የጨፌ ኦሮሚያ ጽህፈት ቤት  ኃላፊ አቶ እንደሻ ብርሃኑ በበኩላቸው፣ የአገር መከላከያ ሰራዊታችን በአገር ላይ የሚቃጣውን ወረራ በጀግንነት ከመመከት ባለፈ የቀጠናው ሰላም እንዲረጋገጥ ታርክ እየሰራ ያለ የአገር አለኝታ ነው ብለዋል። 

የባሌ ዞን ነዋሪዎችም በዞኑ በተደረገው የድጋፍ ሰልፍ ለመከላከያ ያላቸውን አገርነት ከመግለጽ በተጓዳኝ 1 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር ግምታዊ ዋጋ ያላቸው 24  ሰንጋ ለመከላከያ ሰራዊት ድጋፍ አድርገዋል። 

በኢሉባቦር ዞን መቱ ከተማና አካባቢዋ በተደረጉት ሰልፎችም ተሳታፊዎቹ ከሀገር መከላከያ ጎን በመቆም ማንኛውንም ድጋፍ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል።

የድጋፍ ሰልፉ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የኢሉባቦር ዞን አስተዳዳሪ አቶ እንዳልካቸው ተፈሪ የኢትዮጵያ ሀገር መከላከያ ሰራዊታችን የሀገር ክብርና የብሔራዊ ሉዓላዊነት ምልክት፣ የእውነተኛ ሀገር ፍቅርና ጠንካራ የሀገር ወዳድነት ተምሳሌትም ነዉ በማለት ተናግረዋል። 

በዱር በገደሉ እየተዋደቀ ሀገራችን ኢትዮጵያን ከውስጥና የውጭ ጠላቶች በመጠበቅ እኛ ሕዝቦቿም በዓለም አደባባይ አንገታችንን ቀና አድርገን እንድንቆም ውድ የሕይወት የከፈለልን ጋሻችንና የሉዓላዊነታችን መሰረት ጀግናው የሀገር መከላከያ ሰራዊታችን ትልቅ ክብር ይገባዋል ሲሉም ገልፀዋል።

በተመሳሳይ የምዕራብ ወለጋ ዞን ነዋሪዎች ለሀገር መከላከያ ሠራዊት ያላቸውን አጋርነት እና ጽንፈኞቹ እያራመዱት ያለውን እኩይ ተግባር በመቃወም  ሰላማዊ ሰልፍ አድርገዋል።

የዞኑ ዋና አስተዳደሪ አቶ ሰለሞን ታምሩ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት ሃገራችን ኢትዮጵያ ለውስጥና  ለወጪ ጠላቶች ሳትንበረከክ በቁርጥ ቀን ልጆቿ በጀግኖች የመከላከያ ሠራዊታችን ተጠብቃ ዛሬ ደርሳለች ብለዋል፡፡

አቶ ሰለሞን አክለውም ጀግናዉ ሰራዊታችን የሀገር ህልውና ከማስጠበቀ ጎን ለጎንም በልማት ስራዎች አሸራዎቻቸውን በማኖር የሃገሪቱ የብልጸግና ጎዞ አንዲፋጠን የበኩላቸውን ድርሻ እየተወጡ ያሉት የቁርጥ ቀን ልጆች ናቸው ብለዋል፡፡

የምስራቅ ቦረና ዞን ነዋሪዎችም ለመከላከያ ሰራዊት ባደረጉት የድጋፍ ሰልፍ የሀገር መከታ የሆነውን መከላከያ ሰራዊት ስም የሚያጠፉ ጽንፈኞች ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ ጠቀዋል፡፡

በህዝብ የተመረጠው መንግስት ሀገር ለማፍረስ ሌት ተቀን የሚሰሩ ጽንፈኞችን ለህግ እንዲቀርቡም ተጠይቋል፡፡

የነገሌ ቦረና ከንቲባ አቶ አለማየሁ በላይ በዚሁ ጊዜ ሰራዊቱ የውስጥና የውጭ ጠላቶችን የመመከት ልምድና ብቃት ያለው መሆኑን በተግባር ያስመሰከረ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ሰራዊቱ ከዚህም አልፎ ሀገር ለማፍረስ የተነሱ ጠላቶችን አሳፍሮ በመመለስ በአጥንትና በደም ሀገር የገነባ እንደሆነ አስታውሰዋል፡፡

የዞኑ ነዋሪዎችና ሰልፈኞች ለሀገር መከላከያ ሰራዊቱ ከ350 ሺህ ብር በላይ ግምታዊ ዋጋ ያላቸውን አምስት የቦረና ሰንጋዎች አበርክተዋል፡፡

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም