ቀጥታ፡

የአገር መከላከያ ሰራዊት ከፖለቲካ ወገንተኝነት ነፃ ሆኖ የአገርና የሕዝብ አለኝታነቱን በተግባር እያሳየ ነው- ሌተናል ጀነራል ሹማ አብደታ

አዲስ አበባ ግንቦት 20/2015 (ኢዜአ)፡- የአገር መከላከያ ሰራዊት ከፖለቲካ ወገንተኝነት ነፃ ሆኖ የአገርና የሕዝብ አለኝታነቱን በተግባር እያሳየ ያለ ህብረ ብሄራዊ ሰራዊት መሆኑን በመከላከያ ሰራዊት የኮማንዶና አየር ወለድ ዕዝ ዋና አዛዥ ሌተናል ጀነራል ሹማ አብደታ ገለጹ።

በኦሮሚያ ክልል ሸገር ከተማ አስተዳደር በኮዬ ፈጬ ክፍለ ከተማ ነዋሪዎች ለአገር መከላከያ ሰራዊት የድጋፍ ሰልፍ አድርገዋል።

በሰልፉ ነዋሪዎች፣ አባገዳዎች፣ ሀደ ሲንቄዎች፣ የኃይማኖት አባቶችና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች ተሳትፈዋል።

"መከላከያ ሰራዊታችን ኢትዮጵያዊነታችን" በሚል መሪ ሀሳብ ሰልፍ የወጡት ነዋሪዎች ሰራዊቱን በመደገፍ የተለያዩ መልእክቶችን አስተጋብተዋል።
 

ከመልዕክቶቹ መካከል "በመስዋዕትነት እኛን እያኖረ ያለ ሰራዊትን ስም ማጠልሸት ይቁም፣ የኢትዮጵያዊነታችን አርማ የሆነውን መከላከያ ሰራዊት በመተንኮስ የሥልጣን ፍላጎትን ማሳካት አይቻልም፣ የሕዝቦችን ወንድማማችነትና አንድነት የሚሸረሽሩ ሃይሎች በህግ ይጠየቁ" የሚሉና ሌሎችን ይገኙበታል።

በመርሃ ግብሩ ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት የመከላከያ ሰራዊት ኮማንዶና አየር ወለድ ዕዝ ዋና አዛዠ ሌተናል ጀነራል ሹማ አብደታ፤ ሰራዊቱ ከፖለቲካ ወገንተኝነት ነፃ ሆኖ የአገርና የሕዝብ አለኝታነቱን በተግባር እያሳየ ያለ ጀግና ሰራዊት መሆኑን ገልጸዋል።

"የቀደሙት አያቶች በከባድ መስዋዕትነት ኢትዮጵያን አጽንተዋል" ያሉት ሌተናል ጀነራል ሹማ፤ የአሁኑም ሰራዊት ለአገሩ ክብር በፍፁም ጀግንነት መስዋእትነት ለመክፈል ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል።

በመሆኑም የአገር መከላከያ ሰራዊት በየትኛውም መልኩ የአገርና ህዝብን ህልውና የሚፈታተኑ አካላትን በዝምታ የማያልፍ መሆኑን ተናግረዋል።

የሸገር ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ዶክተር ተሾመ አዱኛ፤ የሰላማዊ ሰልፉ ዓላማ ሰራዊቱ አገርን ለማጽናት እየከፈለ ላለው መስዋዕትነት ምስጋና ለማቅረብና ሁልጊዜም ከጎኑ መሆናችንን ለማሳየት ነው ብለዋል።

ሰራዊቱ በአገረ መንግስት ግንባታ ሂደት ጠንካራ አገር እንዲፈጠር ለሚከፍለው መስዋዕትነት ትልቅ ክብር ሊቸረው እንደሚገባም አጽንኦት ሰጥተዋል።

በድጋፍ ሰልፉ ተሳታፊዎች መካከል ለኢዜአ አስተያየታቸውን የሰጡት አቶ ኢፋ ዳዲ እና አቶ አብዱልባስጥ መሀመድ፤ ለሰራዊታችን ምስጋና ከማቅረብ ባለፈ ሁሌም ከጎኑ መሆናችንን ለማረጋገጥ ወደ አደባባይ ወጥተናል ብለዋል።

በዕለቱ ከሸገር ከተማ አስተዳደር ለመከላከያ ሰራዊት የተበረከተውን ስጦታም ሌተናል ጀነራል ሹማ አብደታ ተረክበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም