የህንፃ ግንባታዎች ጥራት ያላቸውና አደጋን የሚቋቋሙ ሆነው እንዲገነቡ ባለድርሻ አካላት ሃላፊነታቸውን እንዲወጡ ተጠየቀ - ኢዜአ አማርኛ
የህንፃ ግንባታዎች ጥራት ያላቸውና አደጋን የሚቋቋሙ ሆነው እንዲገነቡ ባለድርሻ አካላት ሃላፊነታቸውን እንዲወጡ ተጠየቀ
አርባ ምንጭ ግንቦት 20/2015 (ኢዜአ) ፡-የህንፃ ግንባታዎች ጥራት ያላቸውና አደጋን እንዲቋቋሙ ተደርገው እንዲገነቡ ባለድርሻ አካላት ሃላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚገባ የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ባለስልጣን ጠየቀ።
ባለስልጣኑና ተጠሪ ተቋማት በሀገሪቷ ህንፃ ግንባታ ጥራትና ደህንነት ዙሪያ በአርባ ምንጭ ከተማ መክሯል።
በዚሁ ጊዜ የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር መስፍን ላቀው እንዳሉት ባለስልጣኑ ባለፉት 4 ዓመታት በሀገራችን የህንፃ ግንባታዎችን ጥራት ለማወቅ ባደረገው የመስክ ምልከታ ከጥራት፣ ከጊዜ፣ ከደህንነትና ከተፈጥሮ ሀብቶች አጠቃቀም ጋር በተያያዘ ክፍተቶች መኖራቸውን ተገንዝቧል።
በርካታ የህዝብና የሀገር ሀብት የሚንቀሳቀስበት ዘርፉ የሚጠበቅበትን ሚና እንዲወጣ የባለድርሻ አካላት የአሰራር ክፍተቶችን ፈጥኖ የማረም ሃላፊነት እንዳለባቸው ዋና ዳይሬክተሩ አስገንዝበዋል።
መሰል አደጋዎችን መከላከል የሚጀምረው ከዲዛይን ጥራት ጀምሮ መሆኑን በማውሳት።
በአገሪቷ የተፈጥሮ አደጋ ሳይከሰት በጥራት መጓደል ብቻ የህንፃዎች መደርመስ በሰዉና ንብረት ላይ አደጋ ሲያስከትል እንደነበረም አስታውሰዋል።
በመሆኑም እንደ ሀገር የሚካሄዱ ግንባታዎች ያለባቸውን ችግሮች ነቅሶ በማውጣት ትኩረት እንዲሰጥ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል።
ለወደፊቱም የግንባታ ስራዎች ጥራቱ የተጠበቀና አደጋን መቋቋም እንዲችሉ ሆነው እንዲከናወኑ የግንባታው ባለቤቶች፣ አማካሪ ድርጅቶች፣ ተቋራጮችና የህንፃ ሹሞች ድርሻቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።
የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ዳዊት መሀሪ በበኩላቸዉ የግንባታ ሥራዎች ብዙ ተዋናዮች ያሉበት መሆኑን ተናግረዋል።
በመሆኑም እያንዳንዱ ተዋናይ የሚጠበቅበትን ሚና በአግባቡ ካልተወጣ የሚደርሰው አደጋ ቀላል የማይባል ሲሆን ሁሉንም ጠቅልሎ የመጉዳት ዕድሉም ሰፊ መሆኑን ገልጸዋል።
ለዚህም ከዲዛይን ጀምሮ እያንዳንዱ ሂደት በዕዉቀት ላይ የተመሠረተ እንዲሆን ተቋማቸው ለዘርፉ ሙያዊ ስልጠና ከመስጠት ጀምሮ በእያንዳንዱ ተግባራት ላይ ድጋፍ እየሰጠ መሆኑን ጠቁመዋል።