የአማራ ክልል ማረሚያ ቤቶች ኮሚሽን የፖሊስ አባላት ምረቃ እያካሄደ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የአማራ ክልል ማረሚያ ቤቶች ኮሚሽን የፖሊስ አባላት ምረቃ እያካሄደ ነው
ባህር ዳር ግንቦት 20/2015 (ኢዜአ)፦ በአማራ ክልል ለሚገኙ ማረሚያ ቤቶች ኮሚሽን የሰለጠኑ የፖሊስ አባላት በደቡብ ጎንደር ዞን ዓለም በር ጊዜያዊ ማሰልጠኛ ማዕከል የምረቃ ስነ-ስርዓት እየተከናወነ ነው።
በምረቃ ስነ-ስርዓቱ የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ደጀኔ ልመንህ፣ የክልሉ ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ሃላፊ አቶ ደሳለኝ ጣሰው፣ የክልሉ ማረሚያ ቤቶች ኮሚሽን ኮሚሽነር ደስየ ደጀንን ጨምሮ ሌሎች የክልሉና የደቡብ ጎንደር ዞን የስራ ሃላፊዎች ተገኝተዋል።
ተመራቂ የፖሊስ አባላቱ ቀደም ሲል በክልሉ ልዩ ሃይል አባል ሆነው ሲያገለገሉ የቆዩና መንግስት ወደ ሌሎች የፀጥታ ዘርፎች እንዲሰማሩ ያስቀመጠውን አቅጣጫ ተቀብለው የሰለጠኑ መሆናቸው ተገልጿል።
የአማራ ክልል ማረሚያ ቤቶች ምክትል ኮሚሽነር ረዳት ኮሚሽነር ውቤ ወንዴ እንዳሉት ሰልጣኞች በስልጠና ቆይታቸው የታራሚዎች አያያዝና ህግ ማስከበር መስክ ላይ ስልጠና እንዲያገኙ ተደርጓል።
እንዲሁም የስነ ምግባር ግንባታ፣ የታራሚዎች ጥበቃና እጀባ፣ በታራሚዎች ማረምና ማነፅ እንዲሁም መሰል መሰረታዊ ስልጠናዎችን እንዲወስዱ ተደርጓል ብለዋል።
ተመራቂዎቹ ልምድ ያላቸውና ስልጠናውን በብቃት የተወጡ መሆናቸው የማረሚያ ቤቶችን አያያዝና አስተዳደር ለማሻሻል ከፍተኛ ሚና እንደሚኖራቸውም ገልጸዋል።