ቀጥታ፡

የሀገር ዋልታና መከታ የሆነውን የሀገር መከላከያ ሠራዊት ስም ማጠልሸት መቆም አለበት - ሜጀር ጄኔራል አድማሱ አለሙ

አዳማ ግንቦት 20/2015 (ኢዜአ) ፦የሀገር ዋልታና መከታ የሆነውን የሀገር መከላከያ ሠራዊት ስም ማጠልሸት መቆም አለበት ሲሉ የደቡብ እዝ ምክትል አዛዥ ሜጀር ጄኔራል አድማሱ አለሙ አስገነዘቡ።

የአዳማ ከተማና አካባቢዋ እንዲሁም ከምስራቅ ሸዋ ዞን ወረዳዎች የተወጣጡ ነዋሪዎች የአገር መከላከያ ሰራዊትን በመደገፍ ሕዝባዊ ሰልፍ በአዳማ ከተማ እያካሄዱ ነው። 

በሕዝባዊ የድጋፍ ሰልፉ ላይ ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉት በሀገር መከላከያ ሰራዊት የደቡብ እዝ ምክትል አዛዥ ሜጀር ጄኔራል አድማሱ ዓለሙ እንዳሉት መከላከያ የማንም የፖለቲካ ውግንና የለውም የኢትዮጵያ ህዝቦች መከታና ጋሻ  ነው።


 

''እኛ ሁሉንም የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦችን ያለአንዳች ልዩነት እኩል የምናከብር፣ ኢትዮጵያን በክብር እያገለገልን ያለን የሀገሪቷ የመጨረሻ ምሽጎች ነን'' ብለዋል።

ይህም በመሆኑ በተለያየ መንገድ የሀገር ሉዓላዊነት ምልክት የሆነውን የአገር መከላከያ ሰራዊት ስም ማጠልሸት ሊቆም ይገባል ሲሉ አስገንዝበዋል።

''ዛሬ በተለያዩ አካባቢዎች የተደረገልን የድጋፍ ሰልፍ ተልዕኳችንን በብቃት እንድንወጣ ተጨማሪ አቅምና ሞራል የሚሆነን ነው'' ያሉት ሜጄር ጄኔራሉ በዚህም ሠራዊቱ ለህዝቡ ከፍተኛ ክብርና ምስጋና አለው ብለዋል።

የአዳማ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ሃይሉ ጀልዴ፣ የሀገር መከላከያ ሠራዊት የሀገር ሉዓላዊነት ምልክት በመሆኑ የሠራዊቱን ስም ማጠልሸት መቆም አለበት ብለዋል።

የከተማው ህዝብ አሁንም ከሠራዊቱ ጎን በመቆም ያለውን ክብርና ወገናዊነት እያረጋገጠ መሆኑንም ገልጸዋል።

የአዳማ ከተማ ህዝብ ባለው አቅም ሁሉ ከመከላከያ ሰራዊት ጎን ሆኖ ድጋፉን በበለጠ አጠናክሮ እንዲቀጥል አሳስበዋል።

የምስራቅ ሸዋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አባቡ ዋቆ በበኩላቸው የዞኑ ሕዝብ ከመከላከያ ሰራዊት ጠንካራ ድጋፍ እንዳለው ገልጸዋል።

መከላከያ ሰራዊት ኢትዮጵያ ፀንታ ለዛሬዋ ቀን እንድትበቃ ወድ ህይወቱን ሲገብር የኖረ በመሆኑ የምስራቅ ሸዋ ዞን አሁንም በሙሉ አቅሙ ከሰራዊቱ ጎኑ እንዲቆም አሳስበዋል።

ሰልፈኞቹ መከላከያ ምትክ የሌላት ወድ ህይወቱን እየገበረ ሀገርን እያኖረ በመሆኑ መከላከያን ማጠልሸት፣ እሱ ላይ በመተኮስ የስልጣን ጥማት ማሳካት አይቻልም፣ የህዝቦችን አንድነትና ወንድማማችነትን የሚሸረሽሩ ፅንፈኞች በህግ ይጠየቁ የሚሉ መፈክሮች አስተጋብተዋል።

እንዲሁም ሠራዊቱን ማጠልሸት ይቁም፣ የኦሮሞ ህዝብ ከሌሎች ኢትዮጵያዊያን ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ጋር በፍቅር የሚኖር ሕዝብ ነው የሚሉ መፈክሮች አሰምተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም