በራያ ቆቦ ወረዳ ሮቢት ከተማ በ15 ሚሊዮን ብር የተገነባው የአካል ጉዳተኞች አዳሪ ትምህርት ቤት ለአገልግሎት ዝግጁ ሆነ - ኢዜአ አማርኛ
በራያ ቆቦ ወረዳ ሮቢት ከተማ በ15 ሚሊዮን ብር የተገነባው የአካል ጉዳተኞች አዳሪ ትምህርት ቤት ለአገልግሎት ዝግጁ ሆነ

ወልዲያ ግንቦት 19/2015 (ኢዜአ) በሰሜን ወሎ ዞን ራያ ቆቦ ወረዳ ሮቢት ከተማ በ15 ሚሊዮን ብር የተገነባው የአካል ጉዳተኞች አዳሪ ትምህርት ቤት ዛሬ ተመርቆ ለአገልግሎት ዝግጁ ሆነ።
አዳሪ ትምህርት ቤቱ አማራ መልሶ መቋቋምና ልማት ድርጅት (አመልድ) ክርስቲያን ብላይንድ ሚሺን (ሲቢኤም) ኢታሊ ከተባለ መንግሥታዊ ካልሆነ ድርጅት ጋር በመተባበር መገንባቱ ተገልጿል።
የአመልድ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ዓለማየሁ ዋሴ እንዳሉት የአዳሪ ትምህርት ቤቱ የተገነባው የአካል ጉዳተኛ ተማሪዎችን ፍላጎት መሰረት አድርጎ ውጤታማ እንዲሆን ታስቦ ነው።
ግንባታው በ2011 ዓ.ም የተጀመረ ቢሆንም በኮቪድ-19 ዓለም አቀፍ ወረርሺኝና በጦርነቱ ምክንያት ተቋርጦ በዚህ ዓመት እንደገና ተጀምሮ ዛሬ ለአገልግሎት ዝግጁ መሆኑን ገልጸዋል።
አክለውም ትምህርት ቤቱ አራት የመማሪያ፣ አስር የማደሪያ፣ አስር የመፀዳጃና አንድ የመመገቢያ እንዲሁም አራት በኤሌክትሪክና በእንጨት የሚሰሩ የማብሰያ ክፍሎችን ያካተተ መሆኑን ተናግረዋል።
በተጨማሪም የውስጥ ለውስጥ መንገድ፣ የልብስ ማጠቢያ ገንዳ፣ የመብራትና የውሃ መስመሮች ግንባታ እንዲሁም 3ሺህ ሊትር የመያዝ አቅም ያለው የውሃ ታንከር ይገኝበታል ብለዋል።
የራያ ቆቦ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሞላ ደሱ በበኩላቸው አመልድ እና ሲቢኤም ኢታሊ በመተባበር የተገነባው ትምህርት ቤት በአካባቢው የሚገኙ አካል ጉዳተኞችን ችግር የፈታ መሆኑን ገልጸዋል።
ትምህርት ቤቱ በዚህ መልኩ መገንባቱም አካል ጉዳተኞች ቀደም ሲል ይገጥማቸው የነበረውን ችግር የፈታ መሆኑን ጠቅሰዋል።
አሁን ያልተሟሉ የተማሪዎች መቀመጫ ወንበርና ዴስኮችን የወረዳ አስተዳደሩ አሟልቶ ትምህርት ቤቱ ለመጪው የትምህርት ዘመን ዝግጁ እንደሚሆንም አስታውቀዋል።
የአማራ ክልል የአካል ጉዳተኞች ሥራ አመራር ቦርድ አባል ወይዘሮ ሰውሐረግ ጌታቸው እንዳሉት በአገራችንም ይሁን በክልላችን አካል ጉዳተኞችን በየዘርፉ የማሳተፍ ስራ ዝቅተኛ ነው።
ለዚህ ዋናው ምክንያት አካል ጉዳተኞች መሰረተ ልማት ተማልቶላቸው በሚፈለገው ደረጃ ወደ ትምህርት ገበታ እንዲገቡ ያለመደረጉ እንደሆነም ገልፀዋል።
በዚህም አመልድ ከሲቢኤም ኢታሊ ጋር ተባብሮ ትምህርት ቤቱን በሮቢት ከተማ ደረጃውን በጠበቀ አግባብ ገንብቶ ለአገልግሎት ማብቃቱ ያስመሰግነዋል ብለዋል።
በክልሉ የመጀመሪያው የሆነው ይኸው አዳሪ የአካል ጉዳተኞች ትምህርት ቤት 55 አካል ጉዳተኞችን ተቀብሎ ከአንደኛ እስከ አራተኛ ክፍል የሚያስተምር መሆኑን አስታውቀዋል።
ተማሪዎች ባለፉት ጊዜያት ጠባብ በሆኑና ቆርቆሮ በቆርቆሮ በተሰሩ የመማሪያ ክፍሎች ተቸግረው ሲማሩ መቆየታቸውን አካል ጉዳተኛ ተማሪ አስረስ አከለ ገልጿል።
''በዚህም ለእኛ አካል ጉዳተኞች የተመቸ ካለመሆኑም ባለፈ በትምህርት አቀባበል ላይ ተፅኖ አሳድሮብን ቆይቷል'' ብሏል።
አሁን ደረጃውን በጠበቀ ትምህርት ቤት እንድንማር ላደረጉን የመንግሥትና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ምስጋና አቀርባለሁ ሲል ተናግሯል።
አዳሪ ትምህርት ቤቱ ቀደም ሲል በህብረተሰቡ ድጋፍና በወረዳ በጀት ተቋቁሞ ለተማሪዎቹ አገልግሎት ሲሰጥ መቆየቱ ታውቋል።