ባንኮች ተወዳዳሪ ለመሆን በሰው ኃይል፣ በቴክኖሎጂና በአደረጃጀት ራሳቸውን በማብቃትና ጠንካራ የካፒታል አቅም መፍጠር አለባቸው - ማሞ ምህረቱ - ኢዜአ አማርኛ
ባንኮች ተወዳዳሪ ለመሆን በሰው ኃይል፣ በቴክኖሎጂና በአደረጃጀት ራሳቸውን በማብቃትና ጠንካራ የካፒታል አቅም መፍጠር አለባቸው - ማሞ ምህረቱ
አዲስ አበባ ግንቦት 19/2015 (ኢዜአ)፦ባንኮች ተወዳዳሪ ለመሆን በሰው ኃይል፣ በቴክኖሎጂና በአደረጃጀት ራሳቸውን በማብቃትና ጠንካራ የካፒታል አቅም መፍጠር እንዳለባቸው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ማሞ ምህረቱ ተናገሩ።
ዘመን ባንክ በአዲስ አበባ በ1 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር ወጪ ያስገነባውን ባለ 36 ወለል የዋና መሥሪያ ቤት ሕንጻ በዛሬው እለት አስመርቋል።
በምርቃ ሥነ-ሥርዓቱ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ማሞ ምህረት አሁን ላይ በኢትዮጵያ በአጠቃላይ 11 ሺህ የሚጠጋ ቅርንጫፍ ያላቸው 31 ባንኮች መኖራቸውን ገልጸዋል።
የባንክ ቅርንጫፎች መብዛት ከዘመናዊ ቴክኖሎጂ ጋር ተዳምሮ የፋይናንስ ተደራሽነትንና አካታችነትን በማረጋገጥ ለአገር ኢኮኖሚ ግንባታ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከቱ መሆኑን ተናግረዋል።
ባንኮች በአሁኑ ሰዓት ለኢኮኖሚ እድገት ተፈላጊውን የፋይናንስ ኃብት በማሰባሰብ ረገድ ትልቅ አስተዋጽኦ እያበረከቱ መሆኑን ተናግረው ከዚህም በላይ ማደግ ይጠበቅባቸዋል ነው ያሉት።
በተለይም ደግሞ በኢትዮጵያ የውጭ ባለሃብቶች በዘርፉ ሲሰማሩ ከእነርሱ ጋር ተወዳዳሪ ለመሆን የሚያስችላቸውን አቅም ለመገንባት ከወዲሁ መዘጋጀትና ለዚህም መሥራት አለባቸው ብለዋል።
በመሆኑም ቀጣይ ተወዳዳሪነታቸውን ይበልጥ አጠናክረው ለመቀጠል በሰው ሃይል፣ በቴክኖሎጂና በአደረጃጀት ራሳቸውን በማብቃት ጠንካራ የካፒታል አቅም መፍጠር ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።
የዘመን ባንክ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ደረጀ ዘበነ በበኩላቸው ባንኩን የማዘመንና ለደበኞች ምቹ የማደረግ ተግባር በስፋት እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።
የደንበኞችን የአገልግሎት የተቀላጠፈ ለማድረግ በአሁኑ ወቅት አሰራሩን ድጅታላይዝ የማድረግ ተግባር በትኩረት እየተሰራ መሆኑንም ነው ያስረዱት።
የዋናው መሥሪያ ቤት ሕንጻ ግንባታ መመረቅ ተበታትኖ የነበረውን የባንኩን አገልግሎት ወደ አንድ ማዕከል በማምጣት ትልቅ ሚና እንዳለው ጠቁመዋል።
ይህ ደግሞ የደንበኞችን እርካታ ለማሳደግ ድርሻው የጎላ እንደሚሆን በመጠቆም።
ዘመን ባንክ የኢትዮጵያን የባንክ ኢንዱስትሪ ሲቀላቀል 149 ነጥብ 6 ሚሊየን የተፈረመና 87 ነጥብ 2 ሚሊየን የተከፈለ ካፒታል እንደነበረው ተመልክቷል።
በአሁኑ ወቅት የተከፈለ ካፒታሉን ሕጋዊ መጠባበቂያውን ሳይጨምር ወደ 5 ቢሊየን ብር ማሳደጉ የቻለ ሲሆን ባንኩ በቀጣይ አምስት ዓመታትም የባንኩን ካፒታል ወደ 15 ቢሊየን ብር ለማድረስ እቅድ ይዞ እየሰራ ነው።
ዘመን ባንክ በተማሪዎች ምገባ፣ በአረንጓዴ አሻራ፣ በሰብዓዊ ድጋፍና በሌሎች ዘርፎች የሚጠበቅበትን ማኅበራዊ ኃላፊነቱን እየተወጣ ያለ ባንክ መሆኑ ተመላክቷል።