የኢትዮጵያ ሚድዋይፎች ማህበር የእናቶችና የህፃናትን ሞት ለመቀነስ የድርሻውን እየተወጣ መሆኑን ገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ሚድዋይፎች ማህበር የእናቶችና የህፃናትን ሞት ለመቀነስ የድርሻውን እየተወጣ መሆኑን ገለጸ
ሐረር፤ ግንቦት 19 /2015(ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ ሚድዋይፎች ማህበር ከተለያዩ ባለድርሻና አጋር አካላት ጋር በመቀናጀት የእናቶችና የህፃናትን ሞት ለመቀነስ የድርሻውን እየተወጣ መሆኑን ገለጸ ።
ማህበሩ 31ኛ አለም አቀፍ የሚድዋይፎች ቀን ዛሬ በሐረር ከተማ አከብሯል፡፡
የኢትዮጵያ ሚድዋይፎች ማህበር ፕሬዚዳንት ዶክተር ሰለሞን ሃይለመስቀል በወቅቱ፤ ባለፉት ዓመታት ለሚድዋይፎች በተሰጠው ትኩረት የህፃናትና የእናቶችን ሞት መቀነስ መቻሉን ተናግረዋል፡፡
አሁንም ለዘርፉ ትኩረት በመስጠት ተጨማሪ ስራዎችን በማከናወን የእናቶች እና ህፃናትን ሞት የመቀነሱ ጉዳይ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ አመልክተዋል።
ማህበሩ አሁንም ከተለያዩ ባለድርሻና አጋር አካላት ጋር በመቀናጀት የድርሻውን እየተወጣ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
በሀገሪቱ የሚድዋይፎች ብዛት ከእናቶች ቁጥር ጋር ሲነፃፀር ተመጣጣኝ አለመሆኑን የጠቆሙት ዶክተር ሰለሞን፤ ሚድዋይፎችን በበቂ ብዛትና ጥራት በማሰልጠን ማሰማራት እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል፡፡
በሌላ በኩል ከእናቶች ቅድመ ወሊድ ጀምሮ እሰከ ድህረ ወሊድ ድረስ ያልተቆራረጠ ጥራቱን የጠበቀ ክትትል እንዲያገኙ በጤና ጣቢያዎች ያሉ የጤና የመሰረተ ልማት ግብአቶች ተመጣጣኝ ሊሆኑ ይገባል ብለዋል፡፡
በተለይ አገልግሎቱን ለማዘመን ሚድዋይፎች የሚሰለጥኑባቸው የትምህርት ተቋማት ጥራትና ብቃት መፈተሸ ብሎም ድጋፍ እና ክትትል ሊደረግ ይገባል ሲሉም ጠቁመዋል፡፡
የጤና ሚኒስቴር የሰው ሃብት ልማት ዳይሬክተር አቶ አሰግድ ሳሙኤል በበኩላቸው፤ የጤና አገልግሎት ጥራትና ተደራሽነትን ለማረጋገጥ ሚኒስቴሩ በትኩረት እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡
የጤና ባለሙያዎችን ተደራሽ ከማድረግ ባሻገር የተመቻቸ የስራ ቦታን ለመፍጠር ጥረት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
የሐረሪ ክልል ጤና ቢሮ ሃላፊ አቶ ያሲን አብዱላሂ ፤ ሚድዋይፎች የእናቶችና ጨቅላ ህፃናት ህክምናን በማሻሻል ብሎም በስነ ተዋልዶ ጤና አገልግሎት የላቀ አስተዋጽኦ እያበረከቱ እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡
በክልሉ ብሎም በሀገሪቱ የእናቶችና ህፃናት ሞትን በመቀነስ ተጨባጭ ለውጥ መመዝገብ መቻሉን አመልክተው፤ ለዚህም የሚድዋይፎች ሚና ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ ሚድዋይፎች ማህበር ዘርፉን በማጠናከር የጀመረውን ስራም በተለይ የባለሙያችን አቅም በመገንባትና ጥራት ያለው አገልግሎት እንዲሰጡ በማስቻል የጀመረውን እንቅስቃሴ አጠናክሮ እንዲቀጥል መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
የማህበሩ አመራርና አባላት በጤና ተቋማት አገልግሎት እየሰጡ ከሚገኙ የሚድዋይፎች ጋር በሐረር የጤና ተቋማትን ተዘዋውረው በመጎብኘት ጭምር ቀኑን አከብረዋል፡፡
በሥነ-ሥርዓቱ ላይ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል፣ የፌደራልና የክልል እንዲሁም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አመራሮችና የጤና ባለሙያዎች ተሳትፈዋል፡፡