የኢትዮጵያ የዲጂታል ግብርና ፍኖተ ካርታ ወደ ስራ መግባቱን የግብርና ሚኒስቴር ገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ የዲጂታል ግብርና ፍኖተ ካርታ ወደ ስራ መግባቱን የግብርና ሚኒስቴር ገለጸ
አዲስ አበባ ግንቦት 19/2015 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ የዲጂታል ግብርና ፍኖተ ካርታ ወደ ስራ መግባቱን የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ።
በዲጂታል ግብርና ኤክስቴንሽን ለአርሶና አርብቶ አደሮች ቴክኖሎጂን ተደራሽ በማድረግ ምርታማነት ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑንም አመልክቷል።
ሚኒስቴሩ "ዲጂታል ግብርና ለዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ" በሚል መሪ ሀሳብ በሳይንስ ሙዚየም ከዘርፉ የክልል አመራሮች፣ ከልማት አጋሮችና ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አካሂዷል።
የግብርና ሚኒስትሩ ዶክተር ግርማ አመንቴ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ አርሶና አርብቶ አደሩ ምርታማ እንዳይሆን ከሚያደርጉ ችግሮች መካከል የመረጃ፣ የፋይናንስና የግብዓት አቅርቦት እጥረት ተጠቃሽ ነው።
የሜካናይዜሽን አገልግሎት ተደራሽነት ውስንነቶች እና የአየር ንብረት ለውጥ ምርትና ምርታማነትን በመገደብ አሉታዊ ተጽዕኖ ማሳረፋቸውን አመልክተዋል።
እነዚህን ተግዳሮቶች በመቅረፍ የአርሶና አርብቶ አደሩን ምርታማነት ለማሳደግ በመንግስት በኩል ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
ለዚህም ግብርና ሚኒስቴር የኢትዮጵያ የዲጂታል ግብርና ፍኖተ ካርታን በማዘጋጀት በሚያዚያ ወር ወደ ትግበራ ማስገባቱን ነው ዶክተር ግርማ የጠቆሙት።
ፍኖተ ካርታው አርሶና አርብቶ አደሩ ማህበረሰብ የዲጂታል አገልግሎቶችን በመጠቀም ተግዳሮቶችን ተቋቁሞ ምርታማነትን ከፍ እንዲያደርግ ያለመ ነው ብለዋል።
የዲጂታል ግብርና መረጃን ተደራሽ በማድረግ አርሶና አርብቶ አደሮችን ማብቃትን ያለመ መሆኑን ጠቁመው፤ በዘርፉ የማምረት አቅምን ለማሳደግ እየተሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
ዲጂታል ግብርና ትክክለኛና ዘላቂ የመረጃ ትንተና ላይ የተመሰረቱ ፈጣን ውሳኔዎችን በመስጠት ምርትና ምርታማነት እንዲጨምር እንደሚያደርግ አስረድተዋል።
አርሶና አርብቶ አደሩን ባማከለ መንገድ እስካሁን በተተገበረው የዲጂታል ግብርና ውጤት እየተመዘገበ መሆኑን በማመልከት።
የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ማንደፍሮ ንጉሴ በበኩላቸው፤ በዲጂታል የታገዘ የግብርና ኤክስቴንሽንና የምክር አገልግሎት ላይ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
በተለይ ግብርናውን የሚደግፉ የሞባይል ቴክኖሎጂ መተግበሪያዎችን በማበልጸግና በነጻ የስልክ መስመር አርሶ አደሮች አደሮች ተጠቃሚ እንዲሆኑ እየተደረገ እንደሚገኝ አመልክተዋል።
በዚህም እስካሁን ሰባት ሚሊዮን አርሶ አደሮች ተጠቃሚ መሆናቸውን ተናግረው በቀጣይ ይህን የበለጠ ተደራሽ ለማድረግ እንደሚሰራ ነው ያመላከቱት።
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ሁሪያ አሊ፤ ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ በሁሉም ዘርፎች ጥረቶች እየተደረጉ ነው ብለዋል።
በግብርናው ዘርፍ የዲጂታል ቴክኖሎጂን ለአርሶ አደሩ በማላመድ ምርትና ምርታማነት እንዲረጋገጥ መንግስት በትኩረት እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
ለተጀመሩ ስራዎች ውጤታማነትም የአርሶ አደሮች የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ግንዛቤ ማደግ ወሳኝ በመሆኑ በጉዳዩ ላይ ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር በትብብር እየተሰራ እንደሚገኝ አመልክተዋል።