አፋጣኝ መፍትሔ የሚያሻው የምርታማነት ፀር

2187

 

(ኤልያስ ጅብሪል)

አሲዳማ አፈር  የአፈሩ ኬሚካላዊ ይዘት ወይም ፒ ኤች (pH) መጠን ከሰባት በታች የሆነ እና የሃይድሮጅን (H+) እና አልሙኒየም (Al+3) ንጥረ- ነገሮች የሚበዙበት አፈር ማለት ነው፡፡

የአፈር አሲዳማነት በሀገራችን በግብርናው ክፍለ ኢኮኖሚ ላይ አሉታዊ ጫና እያሳደረ የሚገኝ የአፈር ለምነት ችግር ሲሆን፤ ከፍተኛ ዝናብ የሚያገኙና በምርታማነታቸው የተሻሉ ናቸው የሚባሉትን የሀገሪቱን አካባቢዎች ጭምር እየጎዳ መሆኑንም ነው መረጃዎች የሚጠቁሙት፡፡

የአፈር ጤንነት ችግሮች በሦስት ዋና ዋና መንገዶች  ይገለፃሉ፡፡ ይኸውም አሲዳማነት፣ የጨዋማነት ችግር የሚነሳበትና  ኮትቻማ/ጥቁር ወይም መረሬ አፈር/ ብሎ ማስቀመጥ እንደሚቻል በግብርና ሚኒስቴር የአፈር ኃብት ልማት የአፈር ጤንነትና ለምነት ዴስክ ኃላፊ  ፋኖሴ መኮንን ይናገራሉ፡፡

በኢትዮጵያ ከ15 ሚሊየን ሄክታር በላይ የሚታረስ መሬት ሲኖር ወደ 7 ነጥብ 5 ሚሊየን ሄክታር መሬት በአሲዳማነት  የተጠቃ  እንደሆነ ነው የጠቀሱት፡፡

አፈር ሰብሎች የሚፈልጓቸውን ንጥረ-ነገሮች በተሟላና በተመጣጠነ መልኩ ሳይዝ ሲቀር ምርታማነት ጥያቄ ውስጥ እንደሚወድቅ አቶ ፋኖሴ ይገልጻሉ። ከዚህ አኳያ በኢትዮጵያ ከ1 ሚሊየን ሄክታር በላይ መሬት በአፈር አሲዳማነት ክፉኛ የተጎዳ በመሆኑ ምርታማነቱ ምንም በሚባል ደረጃ የሚቀመጥ መሆኑን ይጠቁማሉ። 

እፅዋት ከአየር፣ ውሃና የፀሐይ ብርሃን በተጨማሪ 18 ዓይነት ንጥረ-ነገሮችን ከአፈር ውስጥ ሊያገኙ እንደሚችሉ ነው ኃላፊው የገለጹት፡፡

የአፈር አሲዳማነት መንስኤዎች

አሲዳማነት በአንድ ጊዜ ተፈጥሮ የሚቆይ ሳይሆን በሂደት እየጨመረ እና እየተስፋፋ የሚሄድ ክስተት ነው፡፡

ለአፈር አሲዳማነት በዋነኝነት የዝናብ መብዛት፣ የአፈር መሸርሸር፣ የሰብል ተረፈ-ምርት ሙሉ በሙሉ ከማሳ ማንሳት እና ፍግ አለመጠቀም፣ እንዲሁም አሲዳማ ዝናብ  የመሳሰሉት አፈር ውስጥ ያሉ ለተክሉ እድገት ጠቃሚ ንጥረ-ነገሮች እንዲሟጠጡ እንደሚያደርግ  በመንስኤነት ይጠቀሳሉ።

የአፈር አሲዳማነት በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች የሚስተዋል ሲሆን ለአብነትም አማራ፣ ኦሮሚያ፣ ሲዳማ፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ ደቡብ እና ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ተጠቃሾች እንደሆኑ  አቶ ፋኖሴ ተናግረዋል፡፡

አሲዳማ አፈርን በኖራ የማከም ዘዴ

አሲዳማ አፈርን ለመከላከል በተፈጥሮና በሰው ሰራሽ መንገዶች ከሚወሰዱ እርምጃዎች ባሻገር አፈሩን በኖራ የማከም ሥራ በዋናነት የሚጠቀስ መሆኑን ነው አቶ ፋኖሴ አፅንዖት ሰጥተው የተናገሩት፡፡

የተለያዩ አፈርን የማከሚያ ግብአቶች ያሉ ቢሆንም በቀላሉ ከመገኘትና ከዋጋው ርካሽነት አንፃር ካልሽየም ካርቦኔት ወይም “ የግብርና ኖራ" እየተባለ የሚጠራው በስፋት አገልግሎት ላይ እንደሚውል ገልጸዋል፡፡

ወደ 15 ነጥብ 6 ሚሊየን ሄክታር የሚታረስ መሬት ሲኖር፤ ከዚህ ውስጥ 7 ነጥብ 5 ሚሊየን ሄክታር ወይም ከ43 በመቶ የማያንሰው በአሲዳማ አፈር የተጠቃ መሆኑን ጠቅሰው፤ ወደ 4 ሚሊየን ሄክታር የሚሆነው በጠንካራ አሲዳማነት የተጠቃ እንደሆነና በኖራ መታከም ያለበት መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ጠንካራ አሲዳማ አፈር ስንል የአፈሩ ኬሚካላዊ ይዘት ወይም ፒ ኤች (pH) መጠን ከ 5 ነጥብ 5 በታች የሆነ እና የሃይድሮጅን (H+) እና አልሙኒየም (Al3+) ካታየኖች የሚበዙበት አፈር ሲሆን፤ የእነዚህ ካታየኖች መብዛት የሰብሎችን ሥር በመመረዝ በዕድገታቸው ላይ አሉታዊ ተጽዕኖን እንደሚፈጥር ነው ከግብርና ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ የሚጠቁመው፡፡

ፒ ኤች መጠኑ ከሰባት ወደ ዜሮ እየቀነሰ ሲሄድ የአሲድነቱ ጥንካሬ የሚጨምር ሲሆን ከሰባት ወደ 14 ሲጨምር የጨዋማነቱ ባህሪ እንደሚጨምር ነው የዘርፉ ባለሙያዎች የሚያስቀምጡት።

በአገራችን ሁኔታ አሲዳማ አፈርን ለማከም ኖራ መጠቀም የሚያስፈልገው የአፈሩ ፒ ኤች መጠን ከ5 ነጥብ 5 በታች ሲሆን ነዉ፡፡ ኖራ በተፈጥሮ የሚገኝ የካልሲየም እና የማግኒዚየም ካርቦኔት ሃይድሮኦክሳይድ ውህድ ሲሆን፤ አሲዳማ አፈር ውስጥ በሚጨመርበት ወቅት አሲዳማ አፈር ውስጥ የሚገኙትን አልሙኒየም እና ሃይድሮጂን አሉታዊ እንቅስቃሴዎችን በመግታት የአፈሩን ፒ ኤች መጠን ከፍ በማድረግ ለእፅዋት እድገት ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል፡፡ 

በአማካይ በአፈር አሲዳማነት የተጎዳ መሬትን ለማከም በሄክታር 30 ኩንታል የግብርና ኖራ እንደሚያስፈልግ ባለሙያዎች ይመክራሉ። 

በአሲዳማነት የተጠቃ መሬት አሲዳማነትን የሚቋቋሙ ሰብሎች ካልተዘሩበት ወይም አፈሩን በኖራ የማከም ሥራ ካልተሰራ የሚሰጠውን የአፈር ማዳበሪያ ከጥቅም ውጭ በማድረግ ለኪሳራ ይዳርገናል ነው ያሉት፡፡

እንደ አኩሪ አተር፣ ካሳቫ፣ አናናስ፣ ዳጉሳ፣ ቡና፣ ሻይ እንዲሁም የስንዴ ዝርያዎች አሲድን የመቋቋም ባህሪ እንዳላቸውም ተመላክቷል፡፡

ግብርና ሚኒስቴር በአሲዳማነት ከተጠቃው 7 ነጥብ 5 ሚሊየን ሄክታር መሬት 4 ሚሊየን ሄክታር የሚሆነውን በአሥር ዓመት ውስጥ ለማከም ዕቅድ የያዘ ቢሆንም በዕቅዱ መሰረት በዓመት 400 ሺህ ሄክታር መሬት ለማከም ወደ 5 ቢሊየን ብር እንደሚያስፈልግ ነው የተናገሩት፡፡

ከበጀት አንጻር ይህን ከፍተኛ የገንዘብ መጠን በየዓመቱ ከመንግሥት ካዝና ማግኘት ከባድ በመሆኑ ከእርዳታ ሰጪ ድርጅቶች፣ ከአጋር አካላት ድጋፍ ለማግኘት እየተሰራ መሆኑን ነው ያስታወቁት።

ምንም እንኳን በአሲዳማነት የተጠቃውን አፈር ማከም ወጪው ከፍተኛ ቢሆንም አፈሩ ሳይታከም በቆየ ቁጥር ከምርት ውጭ የመሆን ዕድሉ እየጨመረ ስለሚሄድ አገርን የሚያሳጣው ዋጋ ከፍተኛ እንደሚሆን በውል መረዳት ያሻል።

በዚህም የአፈር አሲዳማነት ጉዳይ መፍትሔ ካልተሰጠው ምርታማነትን ከ50 በመቶ እስከ 100 በመቶ  ሊያሳጣ እንደሚችል ነው በግብርና ሚኒስቴር የአፈር ኃብት ልማት የአፈር ጤንነትና ለምነት ዴስክ ኃላፊው  ፋኖሴ መኮንን የሚናገሩት፡፡

ከአፈር አሲዳማነት የተነሳ በየዓመቱ ወደ 9 ነጥብ 1 ቢሊየን ብር በኢትዮጵያ ደረጃ በስንዴ ከሚሸፈነው መሬት ብቻ እየታጣ እንደሆነ ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ይጠቁማል፡፡ ይህ በስንዴ ብቻ ከሚሸፈን መሬት የተወሰደ ግምት ሲሆን በገብስ፣ ጤፍ ወዘተ… ቢታሰብ ምን ያህል የምርት ማሽቆልቆል እንደሚያስከትል ማወቅ ይቻላል፡፡

አሁን ባለው ሁኔታ የስንዴ ምርት በአማካይ በሄክታር እስከ 40 ኩንታል ምርት ሊሰጥ ይችላል፤ ሆኖም ግን የአፈር ጤንነቱን በመጠበቅ አስፈላጊውን ግብአት የምንጠቀም ከሆነ በሄክታር 60 ኩንታል በማምረት አገራችን የጀመረችውን ምርትና ምርታማነትን የማረጋገጥ ሥራ ማከናወን ያስችለናል ነው ያሉት፡፡

ይህንንም ከግብ ለማድረስ የግብርና ሚኒስቴር የመጀመሪያው የትኩረት አቅጣጫው የአሲዳማ አፈር ልማት መሆኑን ነው አቶ ፋኖሴ ያስረዱት፡፡ አሲዳማ አፈሩን ለመከላከል በተቀመጠው አቅጣጫ መሠረት ባለፉት ሦስት ዓመታት 38ሺህ 369 ሄክታር መሬት በኖራ የማከም ሥራ መከናወኑ ተገልጿል። ይህ ከሚኒስቴሩ ዕቅድ አኳያ ሲታይ በጣም ዝቅተኛ አፈጻጸም ነው።

የአፈር አሲዳማነትን ለማከም የግብርና ኖራ ምርት ላይ የተሰማሩ አምራች ኢንዱስትሪዎች አቅርቦቱን በሚፈለገው ደረጃ ቢያቀርቡም፤ የኖራ ምርቱ በብዛት ያለበት ቦታ እና አሲዳማ መሬቱ የሚገኝበት ርቀት በተቃራኒው በመሆኑ ከትራንስፖርት አንጻር ያለው ችግር ሥራውን አድካሚ እንዳደረገው ነው የሚኒስቴሩ መረጃ የሚያመለክተው።

ነገር ግን አርሶ አደሩ አንድ ጊዜ መሬቱን በኖራ ማከም ከቻለ እስከ አምስት ዓመት ሊያገለግለው ይችላል። ከዚያም በኃላ ቢሆን የተወሰነ የምርት መቀነስ እንጂ በምርታማነት ላይ የጎላ ችግር አይኖረውም ነው ያሉት።

ስለሆነም ኖራን የመጠቀም ሁኔታ አቅም ያለው አርሶ አደር በግዥ መልክ እንዲጠቀም፤ አቅም የሌለው ደግሞ መንግሥት ድጋፍ በማድረግ ተጠቃሚነታቸውን ማረጋገጥ ያስፈልጋል ብለዋል።

እንደ ምዕራብ ኦሮሚያ ነጁ፣ መንዲ፣ ምዕራብ ወለጋ እንዲሁም በአማራ ክልል አዊ ዞን፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አብዛኛውን ወረዳዎች በአፈር አሲዳማነት ክፉኛ የተጠቁ በመሆናቸው ምርት ለመስጠት የማይችሉበት ደረጃ ላይ እየደረሱ መሆኑን አቶ ፋኖሴ ገልጸዋል።

ዝዋይ፣ ሐዋሳ፣ መራቤቴ፣ ደጀን፣ ጉደርና የመሳሰሉት በመንግሥትም ሆነ በግል የግብርና ኖራ ምርት የሚቀርብባቸው ቦታዎች መሆናቸው ነው የተጠቆመው። በእነዚህ ቦታዎች የምርትና የጥሬ ዕቃ ችግር የሌለና የግብርና ኖራ ዋጋም በኩንታል እስከ 350 ብር እየተሸጠ ነው ብለዋል።

የአፈር አሲዳማነት በረዥም ጊዜ የተፈጥሮ መዛባት ሂደት ውስጥ የሚከሰት እንደመሆኑ መጠን አንዴ ችግሩ ከተከሰተ በኋላ መፍትሔ በመስጠት ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ከፍተኛ ወጪ እና ርብርብ የሚጠይቅ ጉዳይ ነው፡፡ 

በመሆኑም ችግሩ ከመከሰቱ በፊት የአፈር አሲዳማነትን ለመከላከል የሚያስችሉ እርምጃዎችን መውሰድ ተገቢነት ያለው ጉዳይ እንደሆነ ነው የተጠቆመው፡፡

መንግሥት በያዘው የሌማት ትሩፋትና የግብርና ኢኮኖሚ አቅጣጫ በተለይም የስንዴ ምርት ከራስ ፍጆታ አልፎ ለሌሎች አገራት ምርቱን በመላክ የውጭ ምንዛሬ ለማግኘት በሚደረገው ጥረት የአፈር ምርታማነትን/ጤንነቱን መጠበቅ ቅድሚያ የሚሰጠው ተግባር መሆኑ የግድ ነው።

“ለም አፈር በሌለበት ምርትና ምርታማነት የማይታሰብ ነው” የሚሉት አቶ ፋኖሴ፤ ግብርና የመሪነት ተግባሩን እንዲወጣ በቅድሚያ የአፈር ጤንነት ሊጠበቅ ይገባል ብለዋል።

በመሆኑም ከዚህ በፊት ያለውን የግንዛቤ ችግርና ከአመራሩ እስከ አርሶ አደሩ ያለውን ክፍተት በመቅረፍ ችግሩን ለመቀነስ እየተሰራ እንደሚገኝም አክለዋል።

ሁሉንም ነገር ከመንግሥት መጠበቅ የለብንም የሚሉት አቶ ፋኖሴ፤ በቅድመ-መከላከል ሥራ ችግኝ በመትከል፣ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራ በማከናወን፣ በተፈጥሮ ማዳበሪያ (ኮምፖስት) የራስን ማሳ በመንከባከብ፣ አማራጭ ሰብሎችን እያፈራረቁ በመዝራት፣ አሲዳማነትን መቋቋም የሚችሉ ተክሎችን በመምረጥ ማልማት  እንዲሁም የግብርና ኖራ በመጠቀም የድርሻችንን ልንወጣ ይገባል ሲሉ አብራርተዋል። 

በሀገራችን በተለያዩ የምርምር ተቋማት የተሰሩ ምርምሮች እንደሚያሳዩት አሲዳማ አፈርን ለማከም የተፈጥሮ ማዳበሪያዎችን ከኖራ ጋር አቀናጅቶ በመጠቀም በዋና ዋና ሰብሎች ላይ እስከ ሁለት እጥፍ የምርት ጭማሪ ማግኘት እንደሚቻል ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

በመሆኑም አርሶ አደሮች ኖራ በግዥና በብድር የሚያገኙበትን ሥርዓት በተጠናከረ አግባብ መተግበር ያስፈልጋል። ልክ እንደ ማዳበሪያና ምርጥ ዘር በግዥ ወይም በብድር የግብርና ኖራ በማቅረብና በአሲዳማነት የተጎዳው መሬት እንዲያገግም ማድረግ ላይ አትኩሮ መስራት ሌላው የመፍትሄ አካል ተደርጎ መወሰድ ይኖርበታል።

የእርሻ መሬት አያያዝና እንክብካቤ ጉዳይ የህግ ማዕቀፍ ኖሮት በዚያ አግባብ ተግባራዊ ማድረግም በተለይ በአሲዳማነት የመጠቃት አዝማሚያ የተጋረጠበትን የእርሻ መሬት ለመታደግና የተጎዳውንም እንዲያገግም ለማከም የሚሰሩ ስራዎችን ውጤታማ ለማድረግ የሚያግዝ በመሆኑ ልዩ ትኩረት ያስፈልገዋል።

ከዚህ ባለፈም በአንድ የእርሻ ቦታ ላይ የተለያዩ ሰብሎችን መዝራት፣ አፈር ውስጥ ህይወት ያላቸው ነገሮች እንዲኖሩ ማድረግና የአፈሩን እርጥበታማነት ማዝለቅ ተገቢ ይሆናል። 

 

 

 

   

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም