ቀጥታ፡

በድሬዳዋ ለነባርና አዳዲስ ኢንዱስትሪ ግንባታ ማስፋፊያ ሥራ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ነው - ከተማ አስተዳደሩ

አዲስ አበባ ግንቦት 19/2015(ኢዜአ) በድሬዳዋ ለነባርና አዳዲስ ኢንዱስትሪ ግንባታ ማስፋፊያ ሥራ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን የከተማ አስተዳደሩ ንግድ፣ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ገለጸ።

የድሬዳዋ ንግድ፣ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ አብዲ ሙክታር ለኢዜአ እንደገለጹት በታሪክ አጋጣሚ ድሬዳዋ ከተማ የኢንዱስትሪ ማዕከል ነበረች።

ከተማዋ በታሪክ አጋጣሚ ባለቤት የነበረችበትን የኢንዱስትሪ ማዕከልነት ለማስቀጠል አስተዳደሩ የተለያዩ ሥራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

ለዚህም አዳዲስ ኢንዱስትሪዎችን በመገንባት ነባሮችንም በመደገፍ የማምረት አቅማቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ እየተደረገ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄም አዳዲስ ኢንዱስትሪዎች እንዲከፈቱ፤ ተዘግተው የነበሩ እንደ ድሬዳዋ ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ ያሉ ነባር ፋብሪካዎች እንዲከፈቱ በማድረግ ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ እንደሚገኝ አንስተዋል።

የከተማዋን ኢንዱስትሪ ልማት ውጤታማ ሆነው እንዲቀጥሉም ድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲን ጨምሮ ከባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር መሥራት የሚያስችል ቅንጅታዊ አሠራር ተዘርግቶ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በኢንዱስትሪ የትምህርት ተቋማት ግንኙነትን አጠናክሮ በማስቀጠል አምራች ፋብሪካዎች የሚያጋጥሟቸውን ችግር በጥናት በመለየት መፍትሔ እየተሰጠ መሆኑን ጠቁመዋል።


 

አምራች ኢንዱስትሪዎች ከኃይል፣ ከግብዓት፣ ከመንገድና ከውሃ መሰረተ-ልማት አቅርቦት ጋር እያጋጠሟቸው የሚገኙ ችግሮችን በመለየት ተገቢ የመፍትሔ እርምጃ እየተወሰደ እንደሚገኝ አንስተዋል። 

በተያዘው በጀት ዓመትም ከ120 በላይ አዳዲስ ኢንዱስትሪዎችን በማቋቋም ወደ ሥራ ለማስገባት ዕቅድ ተይዞ በዘጠኝ ወራት ውስጥ ከ90 በላይ የሚሆኑ አዳዲስ አነስተኛና መካከለኛ ኢንዱስትሪዎችን ማቋቋም ተችሏል ብለዋል። 

በከተማዋ የሚገኙ አምራች ኢንዱስትሪዎች ገቢ ምርቶችን በመተካት፣ ወጪ ምርትን በማሳደግ፣ በሥራ ዕድል ፈጠራና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ውጤት እየተመዘገበ መሆኑን ጠቁመዋል። 

በድሬዳዋ ከተማ የተከፈተው ነፃ የንግድ ቀጣናም ለከተማዋ አምራች ኢንዱስትሪዎች መነቃቃትን በመፍጠር ለዜጎች የሥራ ዕድል እየፈጠረ መሆኑን ገልጸዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም