አርሶ አደሩን የባዮ ጋዝ ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ ለማድረግ የሚያስችሉ ሥራዎች ተጠናክረው ቀጥለዋል - ውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር - ኢዜአ አማርኛ
አርሶ አደሩን የባዮ ጋዝ ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ ለማድረግ የሚያስችሉ ሥራዎች ተጠናክረው ቀጥለዋል - ውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር
አዲስ አበባ ግንቦት 19 /2015(ኢዜአ) ፡-አርሶ አደሩን የባዮ ጋዝ ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ ለማድረግ የሚያስችሉ ሥራዎች ተጠናክረው መቀጠላቸውን የውኃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ገለጸ።
ባዮጋዝ ከኦርጋኒክ ቆሻሻ የሚመነጭ ጋዝ ሲሆን ንፁህና ታዳሽ የኃይል አይነት ነው። በዚህ ጋዝ የኤሌክትሪክ ኃይል በተለያዩ መንገዶች ሊመነጭ ይችላል።
ከዚህ በተጨማሪ ባዮ ጋዝ ለማዳበሪያነትም ጭምር የሚያገለግል መሆኑን ነው መረጃዎች የሚያሳዩት።
በኢትዮጵያ የባዮ ጋዝ ልማት የተቀረጸው ፕሮግራም ከተጀመረ 10 ዓመት ማስቆጠሩን ነው በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር የብሔራዊ ባዮ ጋዝ ፕሮግራም አስተባባሪ ተመስገን ተፈራ የሚናገሩት።
ባዮ ጋዝ ለማልማት በተሰራው ሥራ በአገር አቀፍ ደረጃ በተለያዩ ክልሎች የባዮ ጋዝ ቴክኖሎጂዎችን በመገንባት 40 ሺህ የሚደርሱ ቤተሰቦችን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ገልጸዋል።
የባዮ ጋዝ ቴክኖሎጂ ፕሮጀክት ዘጠኝ ክልሎች እየተሰራ እንደሚገኝም ተናግረዋል።
የባዮ ጋዝ ቴክኖሎጂ ፕሮጀክት ግንባታ ሥራም በመንግሥትና በተራድዖ ድርጅቶች አጋርነት በ23 ሚሊየን የአሜሪካን ዶላር እተካሄደ መሆኑን ተናግረዋል።
እስካሁን የፕሮጀክቱ ተጠቃሚ ከሆኑት 40 ሺህ አባወራዎች በተጨማሪ በቀጣይ ከሰባት ዓመት በኋላ ደግሞ ከ165 ሺህ በላይ አባዎራዎችን ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴርም ተራድኦ ድርጅቶችን፣ የግል ኩባንያዎችንና ሌሎች የመንግሥት ተቋማትን በማሳተፍ ፕሮጀክቱን እንደሚያስተባብር ጠቁመዋል።
የባዩ ጋዝ ቴክኖሎጂ የመብራት አገልግሎትን ጨምሮ ለተፈጥሮ ማዳበሪያ፣ ለደን ጥበቃ ሌሎች አገልግሎት መሥጠት የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል።
የባዮ ጋዝ ቴክኖሎጂ የአርሶ አደሩን ሕይወት በማቃለል ከፍተኛ ጠቀሜታ የሚሰጥ መሆኑን በመገንዘብ አገር አቀፍ ፕሮግራም ተቀርፆ እየተሰራ እንደሚገኝ አመላክተዋል።