በጋምቤላ ክልል በአረንጓዴ አሻራ መረሃ ግብር   ከ11  ሚሊዮን በላይ ችግኞች ለመትከል  ዝግጅት  እየተደረገ ነው - ቢሮው

274

ጋምቤላ ግንቦት 19 /2015 (ኢዜአ)፡- ዘንድሮው በሚካሄደው አምስተኛው ዙር   የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር  በጋምቤላ ክልል  ከ11  ሚሊዮን በላይ ችግኞች ለመትከል ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የክልሉ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ቢሮ አስታወቀ።

እየተዘጋጁ ከሚገኙት ውስጥ ከ50 ከመቶ በላይ የሚሆኑት ለሌማት ቱሩፋት ስኬታማነት የሚያግዙ የፍራፍሬ ችግኞች መሆናቸውን ቢሮው ገልጿል።

የቢሮው ኃላፊ አቶ አጃክ ኡቻላ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የተራቆቱ አካባቢዎችን ወደ ቀድሞው ይዞታ በመመለስ ምርታማነትን ለማሳደግ በትኩረት እየተሰራ ነው።

ዘንድሮ በሚካሄደው አምስተኛው  ዙር የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በክልሉ ከ11 ሚሊዮን በላይ ችግኞችን ለመትከል ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ገልጸው፤ እስካሁን ባለው ሂደት ከ10 ሚሊዮን በላይ  ለተከላ መሰናዳቱን አስታውቀዋል።

በክልሉ ዘንድሮ  ከሚተከሉት ችግኞች መካከል ከ50 ከመቶ በላይ የሚሆኑት ኢኮኖሚያዊ  ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞች መሆናቸውን አስረድተዋል።

ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ካላቸው ችግኞች መካከል ማንጎ፣ አቡካዶ፣ ብርቱካንና ፓፓያ እንደሚገኙበት ጠቅሰው፤ እነዚህም የሌማት ቱሩፋት መርሃ ግብርን ስኬታማ ለማድረግ የሚያግዙ  የፍራፍሬ ችግኞች  መሆናቸውን ገልጸዋል።

 ችግኞቹ በ2 ሺህ 496 ሄክታር በተራቆቱ አካባቢዎችና በቤት ጓሮ አካባቢዎች የሚተከሉ ይሆናል ብለዋል።

በክልሉ በአራተኛ ዙር የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር  ከተተከሉት ከ10 ሚሊዮን በላይ ችግኞች መካከል በተደረገላቸው እንክብካቤ 86 በመቶ መጽደቃቸንውም አቶ አጃክ ገልጸዋል።

በጋምቤላ ክልል ባለፉት አራት ዙር የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር  በተተከሉ ከ24 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ ችግኞች ከ17 ሺህ 980 ሄክታር በላይ የተራቆተ መሬት በደን መሸፈን እንደተቻለ ከክልሉ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ቢሮ የተገኘው መረጃ ያሳያል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም