አንጎላ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ግንኙነት በተለያዩ የትብብር መስኮች ለማጠናከር እየሰራች ነው - አምባሳደር ሚጌል ዶሚንጎስ ቤምቤ - ኢዜአ አማርኛ
አንጎላ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ግንኙነት በተለያዩ የትብብር መስኮች ለማጠናከር እየሰራች ነው - አምባሳደር ሚጌል ዶሚንጎስ ቤምቤ
አዲስ አበባ ግንቦት 19/2015 (ኢዜአ) አንጎላ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የረዥም ጊዜ ግንኙነት በተለያዩ የትብብር መስኮች ለማጠናከር እየሰራች መሆኑን በኢትዮጵያ የአገሪቱ አምባሳደር ሚጌል ዶሚንጎስ ቤምቤ ገለጹ።
በኢትዮጵያ የአንጎላ አምባሳደር ሚጌል ዶሚንጎስ ቤምቤ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ የአንጎላና የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እየተጠናከረ መምጣቱን ገልጸዋል።
ይህም ሆኖ ሁለቱ አገራት ያላቸውን ጠንካራ የዲፕሎማሲ ግንኙነት በተለያዩ የትብብር መስኮች ለማጠናከርና አጋርነቱን ለማጎልበት አገራቸው ፍላጎት እንዳላት ነው ያስረዱት።
በተለይም አንጎላ ከኢትዮጵያ ጋር በፋርማሲቲካል፣ አየር ትራንስፖርት፣ ግብርና እና ኢንዱስትሪ ፓርክ የትብብር ዘርፎች ግንኙነቱን ለማጠናከር እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።
በአፍሪካ ምጣኔ ኃብት እድገት ለማምጣት ትልቅ አስተዋጽዖ ባላቸው ግብርናና ኢንዱስትሪ ልማት ላይ ኢትዮጵያ እያከናወነች ያለው ተግባር የሚበረታታ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ኢትዮጵያ በዚህ ዘርፍ ያላትን ልምድ ለመቀመርም አንጎላ እንደምትሻ ነው አምባሳደሩ የተናገሩት።
አንጎላ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ትብብር ይበልጥ ለማጎልበት የሚያስችሉ የሁለትዮሽ ስምምነቶችን ለማድረግ በጋራ እየተሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል።
ሁለቱ አገራት በአፍሪካ ያላቸውን ጂኦ-ፖለቲካዊ አቀማመጥ ለምጣኔ ኃብት እድገትና ልማት ለመጠቀም ትብብራችንን ለማጠናከር እየሰራን ነው ብለዋል።
የሁለቱ አገራት ይፋዊ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የጀመረው እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ1977 መሆኑን መረጃዎች ያመላክታሉ።