ቀጥታ፡

 ወላጆቻቸውን ያጡና በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ዜጎችን  ለመደገፍ የሚያስችል ፕሮጀክት ይፋ ሆነ

 አዲስ አበባ ግንቦት 19/2015(ኢዜአ):- ወላጆቻቸውን ያጡና በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ  5 ሚሊየን  ዜጎችን  ለመደገፍ የሚያስችል ፕሮጀክት ይፋ ሆነ።

"በጎ ፈቃድ ለሀገር ግንባታ" በሚል መሪ ሃሳብ  ሦስት ተቋማት በጋራ ለመሥራት የሚያስችላቸውን የአምስት ዓመት የፕሮጀክት መግባቢያ ስምምነት ተፈራርመዋል።

ስምምነቱን የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅት ባለሥልጣንና አሊያንስ ኬር ፎር ናው የተባለ አጋር ድርጅት ተፈራርመውታል።  

የፕሮጀክት ስምምነቱ ለአምስት ዓመት የሚቆይና በሁሉም ክልሎች የሚተገበር ሲሆን ወደ ትግበራ ሲሸጋገርም 5 ሚሊየን ያህል ዜጎችን በተለያዩ ፕሮግራሞች ተጠቃሚ ለማድረግ ግብ መጣሉ ተገልጿል።  

ፕሮጀክቱን ለማስፈጸም በቀጣዮቹ አምስት ዓመታት 5 ሚሊየን ሀገር በቀል በጎ ፈቃደኞችን ለማሳተፍ ዕቅድ መያዙ ተጠቁሟል።

የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ በሥነ-ሥርዓቱ ላይ እንደተናገሩት፤ በኢትዮጵያ በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ከፍተኛ ቁጥር ያለው ወጣት ተሰማርቷል። 

በየጊዜው በተካሄዱ የማኅበረሰብ ንቅናቄዎች የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በግለሰብ፣ በማኅበረሰብና በተቋም ደረጃ ባህል ሆኖ ተጠናክሮ መቀጠሉን የተናገሩት ሚኒስትሯ፤ ባለፉት ዓመታት በዘርፉ በርካታ ውጤታማ ሥራዎች መሰራታቸውን ገልጸዋል። 

የበጎ ፈቃድ አገልግሎትን በማጠናከር እንዲሁም የሀገር ውስጥ ሰፊ አቅምን በመጠቀም በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ችግሮች ምክንያት የተጎዱ እና በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ዜጎችን ለመደገፍ የሚያስችሉ በርካታ ሥራዎች በቅንጅት እየተሰራ እንደሚገኝም ጠቅሰዋል።

በዛሬው ዕለትም ይፋ የተደረገው ፕሮጀክት በችግር ውስጥ ያሉ ዜጎችን ለመደገፍ እየተደረገ ያለውን ጥረት ይበልጥ ያጠናክረዋል ብለዋል። 

ኢትዮጵያ መደጋገፍንና መተሳሰብን መሠረት ያደረጉ በርካታ ማኅበራዊ እሴቶች ያሏት እንደመሆኑ ይህንን እሴት የበለጠ ማጠናከር እንደሚገባም ተናግረዋል።

በ2014 ዓ. ም  የክረምት መርሃ-ግብር ከ24 ሚሊየን በላይ ወጣቶች በበጎ ፈቃድ ተግባር ላይ መሳተፋቸውን በስምምነቱ ወቅት ተገልጿል። 

የወጣቶች የበጎ ፈቃድ አገልግሎት መርሃ-ግብሮች እንዲሁም ከሌሎች ኢኒሼቲቮች ጋር በማስተሳሰር ለመተግበር በሚደረገው ጥረት ስኬታማነት ሁሉም በጋራ እንዲረባረብ ጥሪ አቅርበዋል። 

በመርሃ-ግብሩ ላይ የመንግሥት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣  አጋር ድርጅቶች፣ የዲፕሎማቲክ ማኅበረሰብ ተወካዮች እንዲሁም  ሌሎች ባለድርሻ አካላት የተገኙ ሲሆን፤ ፕሮጀክቱ ውጤታማ እንዲሆንም የበኩላቸውን እገዛ እንደሚያደርጉ በሰጡት አስተያየት አረጋግጠዋል።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም