ሀገር በቀል ዕፅዋትንና እንስሳትን ጨምሮ የብዝኃ ሕይወት መመናመንን ለማስቀረት ማህበረሰቡን ያሳተፈ የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃን ማጠናከር ይገባል -ተመራማሪዎች

320

 አዲስ አበባ ግንቦት 19/2015(ኢዜአ):- ሀገር በቀል ዕፅዋትንና ብርቅዬ እንስሳትን ጨምሮ የብዝኃ ሕይወት መመናመንን ለማስቀረት ማህበረሰቡን ያሳተፈ የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃን ማጠናከር እንደሚገባ የዘርፉ ተመራማሪዎች ገለጹ፡፡

የኢትዮጵያ ብዝኃ ህይዎት ኢንስቲትዩት በበኩሉ የብዝኃ ሕይወት ሀብቶችን  ጠብቆ ለማቆየት የመገኛ አካባቢያቸውን የማስጠበቅና ዝርያዎችን በማዕከላት የማንበር ተግባራትን እያከናወንኩ ነው ብሏል።

ምሁራኑ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ የሰው ልጅ ሕልውና ዋስትና የሆነው ብዝኃ ሕይወት የሕልውና አደጋ ተደቅኖበታል ብለዋል።

ለብዝኃ ሕይወት አደጋ ለይ መውደቅና መመናመን የኢንዱስትሪ መስፋፋትን እና የህዝብ ቁጥር መጨመርን እንደ ምክንያትነት አንስተዋል፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የብዝኃ ሕይወት ተመራማሪው ፕሮፌሰር ሰብስቤ ደምሰው፤ የአየር ንብረት መዛባት ለብዝኃ ህይወት መመናመን አንዱ መንስኤ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የብዝኃ ሕይወትን ለመታደግ እንደ አረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ያሉ ማህበረሰቡን የሚያሳትፉና ተጠቃሚነቱን የሚያረጋግጡ ተግባራትን ማጠናከርና ግንዛቤን ማስፋት ይገባል ነው ያሉት።

የመሬት ይዞታ አጠቃቀምን ማስተካከልም ሌላኛው ለብዝኃ ህይወት መጠበቅ መፍትሔ መሆኑን አንስተዋል።


 

በሰላሌ ዩኒቨርሲቲ የብዝኃ ሕይወት ተመራማሪ የሆኑት ፕሮፌሰር አየሁ ፈቃዱ እንደሚሉት፤ የህዝብ ቁጥር በፍጥነት እየጨመረ መምጣቱ ለብዝኃ ህይወት መመናመን መንስኤ መሆኑን ተናግረዋል።

አንዳንድ የዕፅዋት ዝርያዎች ለመጥፋት መቃረባቸውን ጠቅሰው፤ይህን ስጋት ለመቀልበስ የብዝኃ ሕይወት ጥበቃ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ብለዋል።

በዚህም አርሶ አደሩ  እየተሳተፈባቸው ያሉ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራዎችን ማጠናከር እንደሚገባ ጠቁመዋል።

የብዝኃ ሕይወት ማገገም ስራ ሲሰራ ከቦታ መረጣ ጀምሮ ማህበረሰቡን ማወያየትና በባለቤትነት እንዲሳተፍ መንግስት በትኩረት እንዲሰራም አመላክተዋል።

በከተማ መስፋፋት፣ በእርሻ መሬት መስፋፋት ምክንያት የመጥፋት አደጋ እየተጋረጠባቸው ያሉት የእንስሳት እና የዕፅዋት ዝርያዎችን ህልውና ለመታደግ፤ በጥናት ላይ የተመሰረተ ልዩ እቅድ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

ለዚህም በምርምር ተቋማት የተካሄዱ ጥናቶችን ወደ ተግባር ማስገባት እንደሚገባ አስረድተዋል።


 

በጅንካ ግብርና ምርምር ማዕከል ተመራማሪ  ምትኩ አየለ በበኩላቸው፤ በተለያዩ ምክንያቶች በደኖች ላይ የሚደርሰው ጉዳት አጠቃላይ ብዝኃ ሕይወት እንዲመናመን እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ይህንን ችግር ለመከላከል በዋናነት ዛፎችን በመትከል እና የአፈር ለምነትን በማሻሻል የደን ሽፋንን ማሳደግ እንደሚገባ ምክረ ሀሳባቸውን ሰጥተዋል።


 

የኢትዮጵያ ብዝኃ ህይዎት ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ፈለቀ ወልደየስ፤ የኢትዮጵያ ብዝኃ ሕይወት ሀብት የሕልውና አደጋ እያጋጠመው መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ኢንስቲትዩቱ ሀገር በቀል ዕፅዋትን እና በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኙ እንስሳትን ጨምሮ የብዝኃ ሕይወት ሀብትን  ጠብቆ ለማቆየት የመገኛ አካባቢያቸውን የማስጠበቅና ዝርያዎችን በማዕከላት የማንበር ተግባራትን እያከናወነ ነው ብለዋል።

 

 

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም