በፕሪሚየር ሊጉ የ26ኛ ሳምንት መርሐ-ግብር ዛሬ ሁለት ጨዋታዎች ይደረጋሉ

370

አዲስ አበባ ግንቦት 19/2015 (ኢዜአ)፦በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ26ኛ ሳምንት መርሐ-ግብር ሁለተኛ ቀን ውሎ ሁለት ጨዋታዎች በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ይደረጋሉ።

መቻል ከሃዋሳ ከተማ ከቀኑ ዘጠኝ ሰአት ላይ ይጫወታሉ።

በሊጉ የደረጃ ሰንጠረዥ መቻል በ33 ነጥብ 9ኛ ሲሆን ሃዋሳ ከተማ በ34 ነጥብ 7ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።

መቻል በፕሪሚየር ሊጉ ባደረጋቸው ያለፉት አምስት ተከታታይ ጨዋታዎች በሁለቱ አሸንፎ በሁለቱ ተሸንፎ በአንዱ አቻ ወጥቷል።

ሃዋሳ ከተማ በበኩሉ ባለፉት አምስት ጨዋታዎች ማሸነፍ አልቻለም። ሁለት ጊዜ ተሸንፎ በሶስቱ ነጥብ ተጋርቷል።

ሁለቱ ክለቦች በመጀመሪያው ዙር ባደረጉት ጨዋታ መቻል 2 ለ 0 ማሸነፉ የሚታወስ ነው።

ሌላኛው የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ26ኛ ሳምንት ጨዋታ አርባ ምንጭ ከተማን እና ኢትዮ ኤሌክትሪክን ከምሽቱ 12 ሰአት ላይ ያገናኛል።

አርባ ምንጭ ከተማ በ26 ነጥብ 14ኛ ደረጃን ይዞ ወራጅ ቀጠና ውስጥ የሚገኝ ሲሆን ቀድሞ ከፕሪሚየር ሊጉ መውረዱን ያረጋገጠው ኢትዮ ኤሌክትሪክ በ12 ነጥብ የመጨረሻውን 16ኛ ደረጃ ይዟል።

አርባ ምንጭ ከተማ በፕሪሚየር ሊጉ ባደረጋቸው ያለፉት አምስት ተከታታይ ጨዋታዎች በአንዱ ሲሸነፍ በአራቱ ነጥብ ተጋርቷል።

ተጋጣሚው ኢትዮ ኤሌክትሪክ ባለፉት አምስት ጨዋታዎች በሶስቱ ሽንፈት የገጠመው ሲሆን ሁለት ጊዜ ደግሞ አቻ ወጥቷል።

አርባ ምንጭ ከተማ የዛሬውን ጨዋታ ካሸነፈ ወልቂጤ ከተማ ጨዋታውን እስኪያደርግ ከወራጅ ቀጠና የመውጣት እድል ያገኛል።

ሁለቱ ክለቦች በመጀመሪያው ዙር ያደረጉት ጨዋታ ሁለት አቻ በሆነ ውጤት መጠናቀቁ የሚታወስ ነው።

በተያያዘ ዜና ትናንት በተደረገ የ26ኛ ሳምንት ጨዋታ ከፕሪሚየር ሊጉ መውረዱን ያረጋገጠው ለገጣፎ ለገዳዲ አዳማ ከተማን 1 ለ 0 በማሸነፍ በሊጉ ሶስተኛ ድሉን አስመዝግቧል።

ተጠባቂው የቅዱስ ጊዮርጊስ እና ባህር ዳር ከተማ ጨዋታ በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም በጣለው ከባድ ዝናብ ምክንያት ሜዳው ማጫወት ባለመቻሉ ላልተወሰነ ጊዜ እንዲራዘም መደረጉ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም