የተፈጥሮ ሃብት አጠቃቀምን በማዘመን በግብርና ምርታማነት ላይ የተመዘገበውን አበረታች ውጤት ማስቀጠል ያስፈልጋል - አፈ-ጉባኤ ታገሰ ጫፎ - ኢዜአ አማርኛ
የተፈጥሮ ሃብት አጠቃቀምን በማዘመን በግብርና ምርታማነት ላይ የተመዘገበውን አበረታች ውጤት ማስቀጠል ያስፈልጋል - አፈ-ጉባኤ ታገሰ ጫፎ
አዲስ አበባ ግንቦት 18/2015 (ኢዜአ):- የተፈጥሮ ሃብት አጠቃቀምን በማዘመን በግብርና ምርታማነት ላይ የተመዘገበውን አበረታች ውጤት ማስቀጠል እንደሚያስፈልግ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ታገሰ ጫፎ ገለጹ።
የደቡብ ክልል ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች እና አርሶ አደሮች ''ከቤተ-ሙከራ እስከ አዝመራ'' በሚል መሪ ሀሳብ በሳይንስ ሙዚየም የተዘጋጀውን የግብርና ሳይንስ አውደ ርዕይ ጎብኝተዋል።
በጉብኝቱም የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ፣ የደቡብ ክልል ምክትል ርዕሰ-መስተዳድር አቶ ተስፋዬ ይገዙ፣ የግብርና ሚኒስቴር፣ የደቡብ ክልል የቢሮ እና የዞን የስራ ኃላፊዎች፣ አርሶ አደሮችና ሌሎች አካላት ተሳትፈዋል።
በጉብኝቱ ወቅት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ- ጉባኤ ታገሰ ጫፎ፣ ግብርና ሰፊውን የኢትዮጵያ ኢኮኖሚያዊ አቅም የሚይዝ የልማት ዘርፍ ነው ብለዋል።
‹‹ከቤተ-ሙከራ ወደ አዝመራ›› በሚል መሪ ሀሳብ የተዘጋጀው የግብርና አውደ ርዕይ በግብርና ምርታማነት የተገኘውን ውጤት ለማስቀጠል ትምህርት የሚሰጥ መሆኑን ገልጸዋል።
በደቡብ ክልል ያለውን ጸጋ በሚገባ በማልማት በሰብል፣ በእንስሳት፣ በአትክልትና ፍራፍሬ የተገኘውን ጅምር የግብርና ልማት ውጤት ማስቀጠል እንደሚገባም በማከል።
መንግስት ለግብርና ምርታማነት ትኩረት በመስጠቱ ከአገር ውስጥ ፍጆታ ባለፈ ለውጭ ገበያ ማቅረብ የተቻለበትን ተጨባጭ ውጤት ማስመዝገብ እንደተቻለ አብራርተዋል።
የግብርና ምርታማነትን በማስቀጠል ዘመናዊ የአካባቢና ውሃ አጠቃቀም ስርዓት በመዘርጋት የተፈጥሮን ሃብትን በአግባቡ ተጠቅሞ የአርሶና የአርብቶ አደሩን ህይወት ማሻሻል ይገባል ብለዋል።
በአረንጓዴ አሻራ፣ በበጋ መስኖ ስንዴና በሌማት ቱሩፋት የልማት ስራ ተጨባጭ ለውጥ መምጣቱን ጠቁመው፤ በግብርና ምርታማነት የተመዘገበው አበረታች ውጤትም ከፍተኛ መነሳሳት መፍጠሩን አንስተዋል።
የደቡብ ክልል ምክትል ርዕሰ-መስተዳድር አቶ ተስፋዬ ይገዙ፤ አውደ ርዕዩ የግብርና ምርታማነት እያስመዘገበ የሚገኘውን ውጤት አመላካች መሆኑን ገልጸዋል።
የግብርና ሜከናይዜሽን እና ኩታ ገጠም የአስተራረስ ዘዴ የምርት እድገትን ለማስቀጠል መሰረት መሆናቸውን ተናግረዋል።
በአውደ ርዕዩም በክልሉ የሚገኙ የእንስሳትና የሰብል ጸጋዎችን በማቀናጀት ምርታማነትን ማሳደግ የሚስችል ትምህርት እንደሚሰጥ አንስተዋል።
የደቡብ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ጥላሁን ከበደ፤ ግብርና የክልሉን አርሶ እና አርብቶ አደር ሕይወት በማሻሻል ተጨባጭ ለውጥ እያስመዘገበ ያለ ዘርፍ መሆኑን ተናግረዋል።
በደቡብ ክልልም ኢትዮጵያን የአፍሪካ የብልጽግና ተምሳሌት ለማድረግ የተያዘውን ራዕይ ለማሳካት ልማዳዊ የግብርና አሰራርን በማሻሻል የምርት እድገትን ለማስቀጠል እየተሰራ እንደሚገኝም ገልጸዋል።
በዚህም ልማዳዊ የማሳ ዝግጅት በማሻሻልና የግብዓት አቅርቦትን በማሳደግ የአርሶ እና አርብቶ አደሩን የምርት እድገት ማሻሻል እየተቻለ እንደሚገኝ አንስተዋል።
አውደ ርዕዩ የኢትዮጵያን እድገትና ብልጽግና ለማሳካት የግብርናው ዘርፍ እያበረከተ ያለውን አስተዋጽኦ ያሳያል ያሉት ደግሞ በደቡብ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የገጠር ልማት ዘርፍ አስተባባሪ እና የግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ዑስማን ሱሩር ናቸው።
በደቡብ ክልልም የተፈጥሮ፣ የሰብል እና እንስሳት ሃብት ጸጋዎችን በማልማት የአርሶ እና አርብቶ አደሩን ምርታማነት ማሳደግ የሚያስችል ውጤታማ የግብርና ልማት ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ፣ ድህነት መሻገር፣ ገቢ ምርትን መተካት፣ ምርትን ለውጭ ገበያ ማቅረብ የስራ እድል መፍጠርና የፋብሪካ ግብዓትን መሙላት የግብርና ልማት ዋነኛ ዓላማ መሆኑን ገልጸዋል።
የግብርና ኤግዚቢሽኑም የአርሶ እና አርብቶ አደሩን ተጠቃሚነት በማሳደግ ከድህነት ወደ ብልጽግና የሚደረገውን ጉዞ ለማሳካት የጋራ ግንዛቤ የሚፈጥር መሆኑን አንስተዋል።
‹‹ከቤተ-ሙከራ ወደ አዝመራ›› በሚል መሪ ሃሳብ በሳይንስ ሙዚየም የተዘጋጀው የግብርና ሳይንስ ኢግዚቢሽን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ መርቀው መክፈታቸው የሚታወስ ነው።