ግብርናን ለማዘመን የተጀመረው ስራ የምግብ ዋስትና ከማረጋገጥ ባለፈ ምርት ወደ ውጭ በመላክ የኢትዮጵያን ታሪክ የሚቀይር ነው-ፕሬዝዳንት ሣሕለወርቅ ዘውዴ - ኢዜአ አማርኛ
ግብርናን ለማዘመን የተጀመረው ስራ የምግብ ዋስትና ከማረጋገጥ ባለፈ ምርት ወደ ውጭ በመላክ የኢትዮጵያን ታሪክ የሚቀይር ነው-ፕሬዝዳንት ሣሕለወርቅ ዘውዴ
አዲስ አበባ ግንቦት 18/2015 (ኢዜአ)፡- ግብርናን ለማዘመን የተጀመረው ስራ የምግብ ዋስትና ከማረጋገጥ ባለፈ ምርት ወደ ውጭ በመላክ የኢትዮጵያን ታሪክ የሚቀይር ነው ሲሉ ፕሬዝዳንት ሣሕለወርቅ ዘውዴ ተናገሩ፡፡
ፕሬዝዳንት ሳሕለወርቅ ዘውዴ በሳይንስ ሙዚየም እየተካሄደ ያለውን የግብርና ሳይንስ ዐውደ ርዕይ ጎብኝተዋል።
ፕሬዝዳንቷ ከገብኝቱ በኋላ በሰጡት መግለጫ እንዳሉት ፤የግብርና ዘርፉን ለማዘመን እየተደረገ ያለው ጥረት 80 በመቶ የሆነው የማሕበረሰብ ክፍል ኑሮን የሚለውጥ ነው።
ጥረቱ የምግብ ዋስትና በማረጋገጥ ረገድ ጉልህ ሚና የሚጫዎት መሆኑንም እንዲሁ፡፡
በዕውደ ርዕዩ የቀረቡ የፈጠራ ስራዎች ዘመናዊ ግብርናን ዕውን ለማድረግ የሚያስችል፣ ወጣቶችና ሴቶች ያቀፈ እና ከከተማ እስከ ገጠር ዘርፉ ትልቅ ትኩረት ተሰጥቶት ውጤታማ ስራ እየተሰራ መሆኑን የሚያሳይ እንደሆነ ገልፀዋል።
ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን በራስ አምርቶ ውጤታማ ለማድረግ የተጀመረውን ጥረትም የሚደነቅ ነው ብለዋል።
በአጠቃላይ ''ግብርና የተሰጠው ትኩረት በልቶ የማያድር ህዝብ በሚል የጠለሸውን የኢትዮጵያ ገፅታና ታሪክ የሚቀይር ነው'' ብለዋል።
የግብርና ሳይንስ ዐውደ ርዕይ በአጭር ጊዜ በዚህ ደረጃ መዘጋጀቱን አድንቀው፣ በዘርፉ መሳተፉ የሚችሉ ህብረተሰብ ክፍሎች መጎብኘት እንዳለባቸው ገልፀዋል።