የቀድሞ የህወሓት ታጣቂ ኃይሎች ተሃድሶና መልሶ የማቋቋም ስራ በይፋ ተጀመረ

አዲስ አበባ ግንቦት 18/2015 (ኢዜአ)፦ የቀድሞ የህወሓት ታጣቂ ኃይሎች የመጀመሪያ ዙር የተሃድሶና መልሶ የማቋቋም ስራ በዛሬው ዕለት በይፋ ተጀምሯል።

የተሀድሶና መልሶ የማቋቋም ስራ በመቀሌ ከተማ "ኩሐ" ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በሚገኝ ጣቢያ ነው የተጀመረው ።

በዚሁ መርሃ ግብር ላይ የብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ብርጋዴር ጀነራል ደርቤ መኩሪያ፤ የተሀድሶና መልሶ የማቋቋም ስራው በፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት መሰረት እንደሚከናወን ተናግረዋል፡፡

በዚህም ለቀድሞ የህወሓት ታጣቂ ኃይሎች የስነ-ልቦና እና የቴክኒክ ስልጠና እንደሚሰጥ ተናግረዋል።

ወደ መደበኛ ህይወት የሚመለሱ ታጣቂዎች የራሳቸውን ህይወት ከመቀየር ባሻገር የክልሉን ልማት ለመደገፍ መስራት እንዳለባቸው ገልጸዋል።

በተጨማሪም የተገኘውን ሰላም ዘላቂ ለማድረግ የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡም እንዲሁ፡፡

መንግስት ከልማት አጋሮች ጋር በመተባበር ወደ ተሃድሶ የገቡ ታጣቂዎች እስኪቋቋሙ ድረስ ዕገዛ እንደሚደረግላቸው ነው የተናገሩት፡፡

የህወሓት ታጣቂ ኃይሎች ተወካይ ብርጋዴር ጀነራል ምግበይ ሀይለ በበኩላቸው የቀድሞ ታጣቂዎቹ የተሀድሶ መርሐ ግብርን አጠናቀው ወደ ህብረተሰቡ ሲመለሱ የልማት ሃይል መሆን እንዳለባቸው ገልጸዋል።

ወደ ተሃድሶ ማዕከል የገቡ የቀድሞ የህወሃት ታጣቂዎችም በሚደረግላቸው ድጋፍ ወደ መደበኛ ህይወት ለመመለስ ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በዚህ የመጀመሪያው ዙር የህወሓት ታጣቂ ሀይሎች ተሀድሶ ማስጀመሪያ መርሃ ግብር ላይ የአፍሪካ ህብረት የሰላም ስምምነቱ ክትትል፣ ቁጥጥር እና ማረጋገጥ ኮሚቴ አባላት ተገኝተዋል።

ዛሬ የተጀመረው መርሀ ግብር የመጀመሪያ ዙር ሲሆን፤ በክልሉ ለዚሁ ስራ የሚውሉ 10 ጣቢያዎች መቋቋማቸውን ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም