ኢትዮ ቴሌኮም ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ስማርት የመማሪያ ክፍል በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ  ስራ አስጀመረ

369

 

አዲስ አበባ ግንቦት 18/2015 (ኢዜአ)፦ ኢትዮ ቴሌኮም ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ስማርት የመማሪያ ክፍል በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በማቋቋም ዛሬ በይፋ ስራ አስጀምሯል።

ኢትዮ-ቴሌኮም በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ስማርት የመማሪያ ክፍሎችን ለማስረጽ የሚያስችለውን ተግባር ለማከናወን ከትምህርት ሚኒስቴርና ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጋር ስምምነት ተፈራርሟል።

በስምምነቱ መሰረት ኢትዮ ቴሌኮም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አራት ኪሎ ካምፓስ ያስገነባው የመማሪያ ክፍል ስራ ጀምሯል።

በኩባንያው እውን የሆነው የስማርት መማሪያ ክፍሎች ዘመናዊ ቴክኖሎጂ የተገጠመላቸው መሆኑ ተገልጿል።

ይህም የመማር ማስተማሩን ሂደት ከተለመደው አካሄድ በተሻለ ቀላል እንደሚያደርገው የተጠቆመ ሲሆን በዚህም ተማሪዎች ከልማዳዊ ትምህርት በማለፍ በተግባራዊ ተሞክሮ የበለጸገና የተሻለ የትምህርት ተሞክሮ እንዲኖራቸው ያስችላቸዋል ተብሏል።

የስማርት ክፍሉ መምህራን በቀላሉ ማስተማር እንዲችሉ እንዲሁም የንድፈ ሃሳብ ትምርቶችን በቴክኖሎጂ ቤተ-ሙከራ እንዲደገፉ ያስችለዋል ነው የተባለው።

ይህም የተማሪዎችን ሁኔታ ለመከታተል ፣የምዘና ፈተናዎችን ለማረምና ውጤቶችን ለማሳወቅ እንደሚያስችል ተመላክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም