ግብርናን በማጠናከር የኑሮ ውድነትን ለማረጋጋትና በዘርፉ የሥራ ዕድል ለመፍጠር በትኩረት እንሰራለን- የዞኖች ዋና አስተዳዳሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
ግብርናን በማጠናከር የኑሮ ውድነትን ለማረጋጋትና በዘርፉ የሥራ ዕድል ለመፍጠር በትኩረት እንሰራለን- የዞኖች ዋና አስተዳዳሪዎች
ሀዋሳ ግንቦት 18/2015 (ኢዜአ) ግብርናን በማጠናከር የኑሮ ውድነትን ለማረጋጋትና በዘርፉ የሥራ ዕድል ለመፍጠር ትኩረት ሰጥተው እንደሚሰሩ በደቡብ ክልል የሃላባ፣ ሃዲያ እና ደቡብ ኦሞ ዞኖች ዋና አስተዳዳሪዎች ገለጹ።
አስተዳዳሪዎቹ ለኢዜአ እንዳሉት የኑሮ ውድነት እና ሥራ አጥነት ችግሮች በየአካባቢያቸው ህብረተሰቡን ለችግር እየዳረጉ በመሆኑ ፈጣን ምላሽ የሚፈልጉ ናቸው።
የክልሉ መንግስት የጉዳዩን አሳሳቢነት በመረዳት በህዝብና ባለድርሻ አካላት ንቅናቄ ችግሩን ለመፍታት ላስቀመጠው የአምስት ወራት ዕቅድ ስኬታማነት ጠንክረው እንደሚሰሩም ተናግረዋል።
በየአካባቢያቸው ያለውን የኑሮ ውድነት ለማረጋጋትና የሥራ ዕድል ለመፍጠር የግብርና ምርታማነትን ማሳደግ ቀዳሚ ሥራ አድርገው እንደሚንቀሳቀሱም ገልጸዋል።
የሃላባ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ዶክተር መሃመድ ኑሪዬ እንዳሉት ባለፉት ዓመታት በዞኑ የተፈጠረው የሥራ እድል ካለው ሥራ አጥ ቁጥር ጋር የተጣጣመ ባለመሆኑ አሁንም ችግሩ ጎልቶ ይታያል።
"የግብርና ሥራውን በማጠናከር የኑሮው ውድነቱን ለማረጋጋትና በዘርፉ የሥራ ዕድል ለመፍጠር በትኩረት ይሰራል" ብለዋል።
በዞኑ ያለውን የውሃ ሃብት በመጠቀም በበጋ የተጀመረውን የስንዴ ልማትን ጨምሮ በአትክልትና ፍራፍሬ ልማት የተጀመረውን ሥራ በማስፋት ለመፍትሄው እንደሚሰራ ገልጸዋል።
የኑሮ ውድነቱን ለማባባስ ምርትን በመጋዝን በሚደብቁ፣ አላስፈላጊ የዋጋ ጭማሪ በሚያደርጉ ህገ ወጦች ላይ ተገቢውን ቁጥጥር በማድረግ ህጋዊ እርምጃ እንደሚወሰድም ዶክተር መሃመድ ገልጸዋል።
"ሥራ እድል ፈጠራና የኑሮ ውድነት የሚገናኙ በመሆናቸው የአካባቢውን ጸጋ በመለየትና ባለድርሻዎችን በማሳተፍ በንቅናቄ ይሰራል" ያሉት ደግሞ የሀዲያ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብርሃም መጫ ናቸው።
"በተለይ የግብርና ምርታማነት ማሳደግ ላይ በትከረት መስራት ይገባል" ያሉት አስተዳዳሪው፣ በዞኑ ስንዴ ድንችና ሌሎች ልማት ሥራዎችን ጨምሮ ያልተነኩ የግብርና አቅሞች እንዳሉ ገልጸዋል።
ግብርናውን ከማዘመን ባለፈ በዕውቀት እንዲመራ በማድረግና በማጠናከር የኑሮ ውድነቱን ለማረጋጋት ከመጠቀም ባለፈ ለሥራ እድል ፈጠራ ለመጠቀም ይሰራል ብለዋል።
ከደቡብ ክልል ወደ ውጭ ከተላከው የስንዴ ምርት ዞኑ የ30 በመቶ ድርሻ እንዳለው የገለጹት አስተዳዳሪው፣ በዘርፉ ያለውን ከፍተኛ አቅም አሟጦ በመጠቀም ሥራ አጥነትንና ኑሮ ውድነትን ለማቃለል ይሰራል ብለዋል።
በከተማና በገጠር ግብርና፣ በሌማት ትሩፋት፣ በከብት እርባታና በሰብል ልማት ዘርፍ የተጀመሩ ውጤታማ ሥራዎችን ማስቀጠል የሚያስችል ሥራ እንደሚከናወንም አቶ አብርሃም ተናግረዋል።
አካባቢው ያሉ ጸጋዎችን በማልማት የኑሮ ውድነትና ሥራ አጥነትን ለመቅረፍ በቅንጅት መስራት ይገባል ያሉት ደግሞ የደቡብ ኦሞ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ንጋቱ ዳንሳ ናቸው።
ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ እንደሚገባ ገልጸው በሥራ ዕድል ፈጠራ ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን በተቀናጀ አግባብ ለመፍታት ይሰራል ብለዋል።
አስተዳዳሪው እንዳሉት በዞኑ በመስኖ የሚለሙ ሰፋፊ መሬቶች፣ የእንስሳት ሃብት፣ የፍራፍሬና ስራስር ምርቶች እንዲሁም ማዕድንና ሌሎች ሃብቶች ይገኛሉ።
ባለሃብቶች እነዚህን ሀብቶች የሚያለሙበትን ዕድል በመፍጠር የአካባቢውን ፀጋ ለሥራ እድል ፈጠራና ኑሮ ውድነት ለማረጋጋት ለማዋል እንደሚሰሩ ተናግረዋል።
የደቡብ ክልል ሥራ እድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዞች ልማት ቢሮ ሃላፊ አቶ ቢረጋ ብርሃኑ በበኩላቸው እንዳሉት፣ በ2015 በጀት ዓመት ባለፉት አስር ወራት ለ347 ሺህ ወጣቶች የሥራ እድል ለመፍጠር ታቅዶ በተከናወኑ ሥራዎች 79 ከመቶ ማሳካት ተችሏል።
በሚቀጥሉት አምስት ወራት በክልሉ በሚካሄድ የሥራ ዕድል ፈጠራ ንቅናቄ ደግሞ ከ134 ሺህ 360 በላይ ዜጎች ተጠቃሚ ለማድረግ ግብ ተይዞ ወደተግባር መገባቱን ተናግረዋል።
በከፍተኛ ትኩረት በሚሰራው የሥራ እድል ፈጠራ ንቅናቄ የግብርናው ዘርፍ ከፍተኛ ድርሻ እንደሚይዝ ገልጸዋል።
በሰብል፣ በፍራፍሬ፣ በእንስሳት ሃብት ልማት፣ የተለያዩ ችግኞን በማፍላት እንዲሁም በመኽር እርሻ ሰፋፊ መሬቶችን ለወጣቶች የሥራ እድል ፈጠራ ለመጠቀም የተቀናጀ ዝግጅት መደረጉን ተናግረዋል።
ሥራ ዕድል ፈጠራና ኑሮ ውድነትን ማረጋጋት ላይ ያተኮረ ክልል አቀፍ የንቅናቄ መድረክ በሃላባ ቁሊቶ ከተማ በቅርቡ መካሄዱ ይታወሳል።