ቀጥታ፡

ኅብረተሰቡ ለታላቁ ሕዳሴ ግድብ በቦንድ ግዢ እንዲሁም በዲፕሎማሲው መስክ የሚያደርገው ድጋፍ ተጠናክሮ ቀጥሏል- ዶክተር አረጋዊ በርሄ

አዲስ አበባ ግንቦት 18/2015 (ኢዜአ)ኅብረተሰቡ ለታላቁ ሕዳሴ ግድብ በቦንድ ግዢ፣ በገንዘብ ስጦታ እንዲሁም በዲፕሎማሲው መስክ የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ መቀጠሉን የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ህዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ብሔራዊ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አረጋዊ በርሄ ገለጹ።

ዋና ዳይሬክተሩ ዶክተር አረጋዊ በርሄ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ ከለውጡ በፊት የግድቡ ግንባታ ሂደት ችግር ውስጥ ገብቶ መቆየቱን አስታውሰዋል።

ሆኖም ከለውጡ ዓመታት ወዲህ በተከናወኑ ሰፋፊ ስራዎች የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ በላቀ ሁኔታ እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።

በለውጡ ዓመታት  የግድቡ ሁለት ተርባይኖች ኃይል እንዲያመነጩ በማድረግ ህብረተሰቡን የሃይል እንዲሁም ሀገርን ከውጭ ምንዛሬ ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል ብለዋል።

በተያዘው በጀት ዓመትም ህብረተሰቡ ለታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የሚያደርገውን ድጋፍ እንዲያጠናክር የሚያስችሉ ስራዎች መከናወናቸውን ዶክተር አረጋዊ ገልጸዋል።

በዚህ ረገድ ከተሰሩ ስራዎች መካከል የግድቡን ወቅታዊ ሁኔታ የሚያሳውቅና የህብረተሰቡን ተሳትፎ የሚያጠናክር “ህዳሴ ቱር“ የተሰኘ የጉዞ መርሐግብር  በተለያዩ ከተሞች መካሄዱን አስታውቀዋል።

ከቦንድ ግዢ ጀምሮ በገንዘብ ስጦታ በተለይም በ8100 አጭር መልዕክት ህብረተሰቡ ለግድቡ ግንባታ ፍጻሜ የሚያደርገው ድጋፍ አጠናክሮ መቀጠሉንም ነው የገለጹት።

በሌላ በኩል የዳያስፖራው ማኅበረሰብ ለታላቁ ህዳሴ ግድብ የሚያደርገው ድጋፍ በልዩ ልዩ መንገዶች ተጠናክሮ መቀጠሉን ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።

የዳያስፖራ ማኅበረሰቡ ከቦንድ ግዢና የገንዘብ ስጦታ በተጨማሪ ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ ያላትን ፍትሐዊ ተጠቃሚነት የሚያሳውቅ ተግባር እያከናወነ እንደሚገኝ ነው ያብራሩት።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም