የአፍሪካ ህብረት የ60 ዓመታት የውጣ ውረድ ጉዞና ቀጣይ የቤት ስራዎች

1535

የአፍሪካ ህብረት የ60 ዓመታት የውጣ ውረድ ጉዞና ቀጣይ የቤት ስራዎች

ሰለሞን ተሰራ

አውሮፓዊያን ለጥቁሮች ከነበራቸው ዝቅተኛ አመለካከት በመነጨ እብሪት “የአፍሪካ ቅርምት” እየተባለ በሚታወቀው አጀንዳቸው አህጉሪቱን ለመከፋፈል ቁጭ ብለው የመከሩት በ18ኛው ክፍለ ዘመን ማገባደጃ ላይ ነበር፡፡

በጀርመን መዲና በርሊን የተሰበሰቡት  ብሪታንያ፣ ፈረንሳይ፣ ስፔን፣ ፖርቱጋል፣ ቤልጂየም እንዲሁም ዘግይተው የተቀላቀሉት ጣልያን እና ጀርመን አቅማቸው የፈቀደውን ያህል አህጉሪቱን በመቆጣጠር  ሀብቷን ለመመዝበር ሕልም አንግበው የወል ቃል ገብተዋል፡፡ 

እነዚህ ሀገራት አፍሪካን አንድ አድርጎ ለመግዛት ሕልማቸውን አስተሳስረው ቢነሱም በመሀከላቸው በነበረው ፉክክር የተነሳ  ምኞታቸው ሳይሳካላቸው ቀርቷል፡፡

አውሮፓውያን በአህጉሪቱ የዘረጉትን የቅኝ አገዛዝ  መዋቅር በጣጥሶ ለመጣል በቅድሚያ አህጉሪቱን አንድ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን የሚያምኑ አፍሪካውያን መሪዎች ህብረት ለመመስረት ቢነሱም ሀሳባቸው ለሁለት በመከፈሉ ሁለት ቡድን እንዲፈጠር ምክንያት ሆኖ አልፏል፡፡

ይህን ተከትሎ የተፈጠሩት ሁለት ቡድኖች በአንድ ወገን ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባው ሀገራቱ በፍጥነት ተዋሕደው አፍሪካ አንድ ልትሆን ይገባል የሚለው የካዛብላንካ ቡድን፤ እንዲሁም አንድ ከመሆን በፊት ሌሎች ትብብሮች ሊቀድሙ ይገባል የሚለው የሞኖሮቪያ ቡድኖች ነበሩ፡፡

ሁለቱም ቡድኖች የአፍሪካ አንድነት እንዲመሰረት ጽኑ አቋም ቢኖራቸውም፣ እንዴት ነው መመስረት ያለበት የሚለው ጥያቄ ግን የልዩነታቸው ወሰን ሆኖ ወደ ንትርክ የገቡበት ጊዜ ነበር።

በ1961 የተመሰረተው የካዛብላንካው ቡድን በጋናዊው ኩዋሜ ኑኩርማህ የሚመራ ሲሆን ዓላማቸው አፍሪካ አሁን መዋሃድ (አንድ መሆን) አለባት የሚል ሲሆን ከአባላቱ መካከል ጊኒ፣ ሊቢያ፣ ግብጽ፣ ሞሮኮ፣ ማሊ፣ አልጄሪያ ይገኙበታል።

የሞኖሮቪያው ቡድን ደግሞ በሴኔጋላዊው መሪ ሴንጎር የሚመራ ሲሆን በስሩም ሃያ አራት ሃገራትን፣ ማለትም ናይጄሪያ፣ ሴኔጋል፣ ካሜሮን፣ አይቮሪኮስት፣ ቶጎ፣ ላይቤሪያ እና ሌሎች ብዙ የፈረንሳይ ቅኝ ተገዥ የነበሩ ሃገራትን ያቀፈ ነበር፡፡

የዚህ ቡድን የውህደት መርህ ደግሞ “አፍሪካ መዋሃድ የምትችለው በኢኮኖሚያዊ ትብብር ሆኖ በቀስታ በምታደርገው ጉዞ ነው” የሚል ነበር፡፡

ይህንን የሁለቱን ወገኖች ፍጥጫ አርግባ ወደ ውህደት ያመጣቻቸው ኢትዮጵያ ስትሆን ድርጅቱ የዛሬ 60 ዓመት እ.ኤ.አ ግንቦት 25 ቀን 1963  ሲመሰረት የመጀመሪያው ሊቀመንበር ሆነው የተመረጡት አጼ ኃይለስላሴ ነበሩ፡፡

የፓን አፍሪካኒዝም ልጅ የሆነው የያኔው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ሲመሰረት ዋና ዋና ዓላማዎቹ ቅኝ ገዢዎችን ማስወገድ፣ በአፍሪካ ሃገራት መካከል አንድነትና ሕብረትን ማበረታታት፣ ለአፍሪካዊያን የተሻለ ህይዎት እና እድገት ለማምጣት፣ ሉዓላዊነትንና የወሰን አንድነትን ማስጠበቅ፣ ሰብዓዊ መብቶችን ማስከበር፣ በአፍሪካ ሃገራት መካከል የሚካሄዱትን ግጭቶች በሰላማዊና በዲፕሎማሲ መፍታት የሚሉ ነበሩ።

የአፍሪካ ህብረት

የአፍሪካ ቀደምት መሪዎች የአፍሪካ አንድነት ድርጅትን የሚተካ አዲስ አህጉራዊ ድርጅት ለመመስረት እ.አ.አ በ1999 ያሳለፉትን ውሳኔ መሠረት በማድረግ የአሁኑ የአፍሪካ ህብረት እ.አ.አ በሐምሌ 2002 በደርባን ደቡብ አፍሪካ በይፋ መመስረቱ ይታወቃል።

የአፍሪካ ኅብረት ራዕይም፤ የተቀናጀች፣ የበለጸገች እና ሰላማዊ፣ በራሷ ዜጎች የምትመራ እና በዓለም አቀፍ መድረክ ላይ ተፎካካሪ የሆነች አፍሪካን መመስረት ነው።

እ.አ.አ በ2013 የአፍሪካ መሪዎች በአፍሪካ ህብረት አማካኝነት አጀንዳ 2063 የተሰኘውን አህጉራዊ እቅድ ነድፈዋል።

እቅዱ ከሁሉም በላይ በአህጉሪቱ ላይ የሚቃጡ ጦርነቶችን ማስቆምና መሰረተ ልማት ዝርጋታ ላይ የሚያተኩር ሲሆን በአህጉሪቱ ዜጎች ከአገር አገር ነፃ እንቅስቃሴ እንዲያደርጉ ራዕይ የሰነቀ ነው።

ሌላው ወሳኝ ፕሮጀክት የአፍሪካ ነፃ ገበያ ምህዳርን መክፈት ሲሆን ይህ የነፃ ገበያ ማዕቀፍ በርካታ አገራትን አሳታፊ በማድረግ የዓለም ትልቁ የነፃ ገበያ ማዕቀፍ ስምምነት ሲሆን አሁን ላይ ተግባራዊ ሊደረግ ከጫፍ ደርሷል።

ይህ የነፃ ገበያ ስምምነት በአፍሪካ አገራት መካከል የሚደረግ ንግድን ለማስፋፋት የታለመ ከመሆኑ በላይ የሀገራቱን ኢኮኖሚ በከፍተኛ ደረጃ እንደሚያሳድገው ታምኖበታል።

የአፍሪካ ነፃ ገበያ ስምምነት አገራት የውስጥ ገበያቸውን ለመጠበቅ ባወጧቸው ቀደምት ህጎችና እንዲሁም በደካማ የትራንስፖርት መሰረተ ልማት ምክንያት ከፍተኛ ችግር እንደሚገጥመው አስተያየት ቢሰጥበትም ያዘለው ተስፋ ግን ከችግሩ የገዘፈ ነው።

ሁሉንም የአፍሪካ አገራት መዲናዎች እና የንግድ ማዕከሎች በፈጣን የባቡር መስመር ማገናኘት፣ በአፍሪካ አገራት መካከል የሚደረግ ንግድን ማበረታታት እንዲሁም የአፍሪካ አገራት በዓለም አቀፍ የንግድ ገበያ ያላቸውን ተሳትፎ ማጎልበት አጀንዳ 2063 ካስቀመጣቸው ግቦች መካከል ቀዳሚዎቹ ናቸው።

አፍሪካውያን በአህጉሪቱ በነፃነት የመዘዋወር፣ የመስራት እና የመኖር መብት እንዲኖራቸው ማድረግ እንዲሁም በአህጉሪቱ ያሉ ግጭቶችን ማስቆም እና ሌሎችም በርካታ ግቦች በእቅዱ ላይ ተቀምጠዋል።

ነገር ግን የአፍሪካ ሕብረት እነዚህን አጀንዳዎች ለማስፈፀም በእጅጉ እየተፈተነ ሲሆን ለዚህ ዋነኛ መንስኤው የሕብረቱ አባል አገራት በገቡት ስምምነት መሰረት ነገሮችን ተግባራዊ እንዲያደርጉ ማስገደድ አለመቻሉ እንደሆነ ይነገራል።

ተንታኞች እንደሚሉት የአፍሪካ አገራት ያለባቸውን ከፍተኛ የእዳ ጫና ለመክፈል የሚያደርጉት ትግል ትልቁን አህጉራዊ አጀንዳ ችላ እንዲሉ ግድ ብሏቸዋል።

የህብረቱ በጎ ርምጃዎች 

የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ሲመሰረት ዋነኛ ዓላማው በቅኝ አገዛዝ ስር የነበሩ ሀገሮችን ነጻ ማውጣት ነበር፡፡ ከዚህ አንጻር የተሳካ ተግባር ማከናወኑ በታሪክ ሲወደስለት የሚኖር ስኬቱ ነው፡፡ የአፍሪካ ህብረትም በብዙ ፈተናዎች ውስጥ ሆኖ ከሞላ ጎደል ውጤት ያስመዘገበባቸው ዘርፎች አሉ። 

ሀ. ሰላምና ደህንነት 

የአፍሪካ ህብረት ሰላምንና ደህንነትን ለማረጋገጥ በተለይም የአፍሪካ የሰላም አስከባሪ ኃይል በተለያዩ የአህጉሪቱ ክፍሎች ያደረገው ተጋድሎ በአዎንታ ሊጠቀስ የሚችል ነው፡፡

ለማሳያም ላይቤሪያ፣ ሴራሊዮን፣ ሶማሊያ፣ ሱዳን ተሰማርቶ የነበረው የአፍሪካ ሰላም አስከባሪ ኃይል ከሌሎች የተሻለ አፈጻጸም እንዳለው ይገለጻል፡፡

ለ. ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት 

በተለያዩ የአፍሪካ አገራት የፖለቲካ መረጋጋት እንዲፈጠር ለማድረግና ዴሞክራሲን ለመገንባት  የሚደረገው ጥረት እና የተፈጥሮ ሃብቷ ለፈጣን ዕድገቱ በምክንያትነት ይነሳሉ፡፡ 

የአፍሪካ ህብረትም በአፍሪካ ንግድና ኢንቨስትመንት እንዲስፋፋና ኢኮኖሚው እንዲያድግ የወሰዳቸው ተቋማዊ እርምጃዎች ወሳኝ ሚና ሲኖራቸው የአፍሪካ ልማት ባንክን በማቋቋም የተለያዩ ፕሮጀክቶችን መደገፉ ተጠቃሽ ነው፡፡ 

በተለይም ለመንገድና ለውኃ ሃይል ማመንጫ ባንኩ ያደረገው ድጋፍ ተገቢው ቦታ የሚሰጠው ሲሆን ለአፍሪካ የእርስ በርስ የንግድ ግንኙነት መሻሻል ማነቆ የሆኑትን ታሪፍ በመቀነስም የተሻለ ስራ ሰርቷል፡፡

ሐ. ዓለም አቀፍ ተሰሚነት 

የአፍሪካ ህብረት በዓለም አቀፍ መድረኮች በተለይም የዓለም ኢኮኖሚንና የአየር ንብረት ለውጥን በተመለከተ አንድ አቋም መያዙ ከህብረቱ ታሪክ ተጠቃሽ ስኬቶች አንዱ ነው፡፡

አፍሪካ የአየር ንብረት ተፅዕኖውን ለመላመድና ለመቋቋም የሚረዳትን ተገቢውን ክፍያ እንድታገኝ ህብረቱ ውጤታማ ስራ ሰርቷል፡፡

የአፍሪካ ህብረት የአፍሪካ የልማት ችግሮችን ለመፍታት ከዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር በትብብር ለመስራት ጥረት አድርጎ ባስመዘገበው ውጤትም ይመሰገናል፡፡ በተለይም የተባበሩት መንግስታት የሚሊኒየም የልማት ግቦች እንደ መገለጫ ይነሳሉ፡፡

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ደግሞ በጸጥታው ምክር ቤት ቋሚ መቀመጫ ለማግኘት እንዲሁም የአፍሪካ ድምጽ የሚጎላበት ሚዲያ እንዲኖር የተጀመሩ እንቅስቃሴዎች በአዎንታ የሚነሱ ናቸው። 

መ. ዴሞክራሲና መልካም አስተዳደር 

የአፍሪካ ህብረት በአህጉሪቱ ዴሞክራሲንና መልካም አስተዳደርን በማስፈን በኩልም ከነጉድለቶቹም ቢሆን በመልካምነት የሚጠቀሱ ስራዎችን እየሰራ መሆኑ ይገለጻል፡፡ 

በአህጉሪቷ ከ30 ዓመት በፊት አምስት ሀገራት ብቻ ዴሞክራት የነበሩ ሲሆን አሁን ከአፍሪካ ሀገሮች 95 በመቶዎቹ ወቅቱን ጠብቀው ምርጫ የሚያካሂዱ ሀገራት ናቸው፡፡ የምርጫ ታዛቢዎችን በአባል ሀገራት እየላከ መታዘቡም እንደ ጥሩ ጅምር መታየት ያለበት ነው፡፡

በተለይ ደግሞ የአፍሪካ የእርስ በርስ መገማገሚያ መድረክን /APRM/ ማቋቋሙ በጥንካሬ ሲነሳ በዚህ መድረክ አማካኝነት ሀገራት በራሳቸው ተነሳሽነት ስለሀገራቸው የመልካም አስተዳደር አፈጻጻም ሪፖርት የሚያደርጉበትና ልምድ የሚለዋወጡበት እድል ተፈጥሯል፡፡

የአፍሪካ ህብረት የአፍሪካ አንድነት ድርጅትን በሀገሮች ውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ያለመግባት መርህ በማሻሻል በመፈንቅለ መንግስት የሚመጡ ቡድኖችን ላለመቀበል መወሰኑ ህብረቱ በዴሞክራሲ ላይ ያለውን አቋም ያሳያል፡፡ 

መሻሻል የሚገባቸው ጉዳዮች 

በርግጥ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ሲመሰረት አንግቦት ከነበረው አባል ሀገራቱን ከቅኝ ገዥዎች ነፃ የማውጣት ተልዕኮ አንስቶ እስከ ወቅታዊው የአየር ንብረት ለውጥ ድርድር አበጀህ የሚያስብሉትን ስኬቶች አስመዝግቧል፡፡

በቀዝቃዛው የዓለም ጦርነት ጊዜ አብዛኛው ሃገራት የገለልተኛ ሀገሮች ማህበር አባል ቢሆኑም የአፍሪካ ሀገሮች እርስ በእርሳቸው ተከፋፍለው አፍሪካን የጦርነት አውድማ አድርገዋት ነበር፡፡ አንዱ የአፍሪካ ሀገር የምዕራቡ ካምፕ ደጋፊ ከሆነ ሌላኛው የምስራቅ ካምፕ ደጋፊ ነበር፡፡ 

ሁለቱም ካምፖች ለርዕዮተ ዓለም ተከታዮቻቸው የጦር መሳሪያ ድጋፍ በማድረግ አፍሪካ እርስ በእርስ እንድትባላ አድርገዋል፡፡ ይህም ህብረቱ የተቀደሰ ሃሳብ ቢኖረውም የማስፈፀም አቅሙ ያን ያህል የተጠናከረ አለመሆኑን ያሳያል፡፡

ለህብረቱ የማስፈጸም አቅም ማነስ አንደኛው ምክንያት ከአባል ሀገራት የሚጠበቀውን ገንዘብ በአግባቡ አለመሰብሰቡ ነው፡፡

መረጃዎች እንደሚያሳዩት የህብረቱ የ2023 በጀት 654 ነጥብ 8 ሚሊዮን ዶላር እንዲሆን በዛምቢያ በተደረገ ጉባኤ ውሳኔ የተላለፈ ሲሆን ከዚህ ውስጥ 60 በመቶ የሚልቀው በጀት ከለጋሾች እንደሚሰበሰብ በወቅቱ ይፋ ተደርጓል፡፡

በሌላ በኩል አፍሪካ በየዓመቱ 50 ቢሊዮን ዶላር በሙስና እንደምታጣ ጥናቶች ያሳያሉ፡፡ ከዚህ ውስጥ 1 በመቶ እንኳን ማዳን ቢቻል የህብረቱን የ2 ዓመት ወጪ መሸፈን ይቻላል ይላሉ ባለሙያዎች፡፡

ጥቂት በማይባሉ የህብረቱ አባል ሀገራት ሙስና ዛሬም አደጋ መሆኑ፣ የርስ በርስ ግጭት በሚፈለገው ደረጃ አለመፈታቱ፣ ድህነት አሁንም የአህጉሪቱ ቀንደኛ ጠላት መሆኑ፣ የትምህርትና ጤና አገልግሎቶች ተደራሽ አለመሆንና ጥራቱም የተጓደለ መሆን፣ በህብረቱ የሚወሰኑ ውሳኔዎች አፈጻጸም የተለያየና የሚፈለገውን ውጤት ከማስመዝገብ አኳያ ውስንነት ያለበት መሆኑ ወዘተ የህብረቱና አባል ሀገራት ጉድለት ሆነው ቀጥለዋል።

ትኩረት የሚያሻቸው ጉዳዮች 

የአፍሪካ ህብረት ከስኬቱም ሆነ ከልምዱ ለመማር የሚያስችለው ከግማሽ ክፍለ ዘመን የዘለቀ የእድሜ ባለፀጋ ሆኗል፡፡ 

እናም የወደፊት አቅጣጫውን ሲተልም ያለፈውን ጉዞ ዞር ብሎ ማየት፤ የቆመበትን ነባራዊ ሁኔታ ጠንቅቆ መረዳትና መጭውን አቅርቦ ማሰብ ይጠበቅበታል። ለዚህ ደግሞ የማስፈጸም አቅምን ማጠናከር፣ ለስራ ዕድል ፈጠራ ትኩረት መስጠት፣ ተሳትፎን ማሳደግ፣ የገቢ አቅምን ማሳደግ ወሳኝ ናቸው። 

ሀ. የማስፈጸም አቅም  

የአፍረካ ህብረት ከአፍሪካ አንድነት ደርጅት የተሻለ አደረጃጀትና አሰራር እንዳለው የሚቀበሉ አሉ፡፡

ለምሳሌ በሀገሮች ጣልቃ ያለመግባት መርህን በማሻሻል ህብረቱ በመፈንቅለ መንግስት የመጡ ቡድኖችን በአባልነት አይቀበልም ነገር ግን በአፍሪካ አሁንም የእርስ በርስ ግጭት የሚታይባቸው ሀገሮች አሉ፡፡ 

ስለሆነም ይህንኑ ችግር ሊቀርፍ የሚችልና ነባራዊ ሁኔታውን ያገናዘበ አደረጃጀትና አሰራር ሊኖረው ይገባል፡፡

የህብረቱ በጀት በሌሎች አካል መሸፈን አሉታዊ ተፅዕኖ ስለሚኖረው አባል ሃገራት የሚጠበቅባቸውን መዋጮ በወቅቱ በመክፈል የህብረቱን የማስፈፀም አቅም ማሳደግም ይጠበቅባቸዋል፡፡

ለ. የስራ እድል ፈጠራ 

የአፍሪካ ህብረት በተለይ ወጣቱን የህብረተሰብ ክፍል ማዕከል ያደረገ እድገትን ማበረታታት ግድ የሚለው ወቅት አሁን ነው፡፡

ሆኖም ፍትሃዊ የሃብት ክፍፍል ከማረጋገጥ አኳያ ብዙ የሚቀሩ ስራዎች እንዳሉ እሙን ነው። በተለይም ወጣቶችን ተጠቃሚ ከማድረግ አኳያ መሰራት ያለባቸው የቤት ስራዎች በአግባቡ አለመሰራታቸው በጉልህ ይጠቀሳሉ፡፡ 

እንደ አፍሪካ ኢኮኖሚ አውትሉክ መረጃ በአፍሪካ እድሜያቸው ከ15 እስከ 25 ዓመት ያሉ ወጣቶች ከአህጉሪቱ አጠቃላይ ህዝብ ከ70 ከመቶ በላይ ይሸፍናሉ፡፡

የዓለም ባንክ ያወጣው መረጃ እንደሚያሳየው በአፍሪካ 200 ሚሊዮን የሚጠጉ እድሜአቸው ከ15 እስከ 25 የሚጠጋ ወጣቶች ሲኖሩ ከነዚህ መካከል 60 በመቶ የሚጠጉት ስራ ፈላጊ መሆናቸው ደግሞ ህብረቱ የሚጠብቀውን ከባድ ስራ ያሳያል፡፡

የአፍሪካ ህብረትም በየሃገሮቹ ለወጣቶች ምን ያህል የስራ እድል እንደተፈጠረ መጠየቅን የእርስ በእርስ መገማገሚያ መድረኩ ዋነኛ የትኩረት አቅጣጫ ሊያደርገው እንደሚገባ ምሁራን ይመክራሉ፡፡

ሐ. የህዝብ ተሳትፎና የውክልና ዴሞክራሲ 

ህብረቱ ሊያሳካ ያሰባቸውን ግቦች እውን ማድረግ የሚቻለው በሁሉም የነቃ ተሳትፎ መሆኑ አያጠያይቅም። በመሆኑም አባል አገራት  ችግሮችን ከመለየት ጀምሮ እስከ ክትትልና ግምገማ ስርአት ህብረተሰቡን በሁለንተናዊ መርሃ ግብሮች ማሳተፍ ይገባቸዋል፡፡ 

ይህ ሲደረግ ነው በተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ውስጥ ያሉ ስፍር ቁጥር የሌላቸው የፈጠራ ችሎታዎችን ማውጣትና ሀገሬ ለእኔ ምን አድርጋለች ሳይሆን እኔ ለሀገሬ ምን አደረግሁ የሚሉ ዜጎችን መፍጠር የሚቻለው፡፡ 

በአፍሪካ በየቦታው የሚታዩ የእርስ በእርስ ግጭቶች መንስኤ በዋነኛነት የህዝብ ፍላጎት አለመሟላት ሲሆን በተለይም የአናሳዎች መብት አለመከበር የግጭት መንስኤ ሲሆን ይታያል፡፡  ለዚህ ደግሞ በየአካባቢው አስተዳደር ህዝቡን በየጊዜው ማማከር ያስፈልጋል፡፡

መ. ውስጣዊ የገቢ አቅምን ማሳደግ 

በዋናነት አራት የገቢ ምንጮች ያሉ ሲሆን እነሱም የሃገር ውስጥ ብድር፤ ግብርና ታክስ፣ የውጭ ብድር እና እርዳታ ናቸው፡፡

ከግብርና ታክስ በስተቀር ሌሎች የገቢ ምንጮች አሉታዊ ተጽዕኗቸው ከፍተኛ ነው፡፡ ስለዚህ ግብርና ታክስን በአግባቡ መሰብሰብ የአንድ ሀገር የሁለንተናዊ ብቃት መለኪያ ነው፡፡ ግብርና ታክስ የመንግስት ወጪ በመሸፈን ነጻነትን ከማጎናጸፉም በተጨማሪ ፍትሃዊ የሃብት ክፍፍልን ለማረጋገጥ ሁነኛ መሳሪያ ነው፡፡

አልጀዚራ ባወጣው መረጃ መሰረት አፍሪካ በእርዳታና በብድር ከምታገኘው ይልቅ በታክስ ማጭበርበርና ስወራ የምታጣው ከ10 እጥፍ በላይ ይበልጣል፡፡

ለዚህ ደግሞ የታክስ ህጎች ክፍተት መኖርና በሙስና የተጨማለቁ ባለስልጣናት እንዲሁም ብቃት ያለው የሰው ኃይል አለመኖር አስተዋፆኦ ያደርጋሉ፡፡ የገቢ አሰባሰብ ስርአቱን በማሻሻል የአፍሪካን ነጻነት ማረጋገጥ ይቻላል፡፡ 

ከዚህ በተጨማሪም የአፍሪካን የእርስ በርስ ንግድ ማስፋፋት፤ የታሪፍና ቀረጥ ምጣኔን ማሻሻል፤ የወጪ ገበያ የምርት አይነቶችን ማስፋትና ሃገራቱን በመሰረተ ልማት ማስተሳሰር የየሃገራቱን የተናጠል ጥረትና የህብረቱን አመራሮች የጋራ ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች ናቸው፡፡

በአጠቃላይ የአፍሪካ ህብረት አባል ሀገራቱን በማስተባበር ባለፉት 60 ዓመታት ያለፈበትን የውጣ ውረድ ጉዞ በማጤን የተሻለ ነገን ለመገንባትና የአፍሪካን ብልጽግና ለማረጋገጥ ከትላንቱ በበለጠ መትጋት ይገባዋል።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም