ኢትዮጵያውያን የታላቁን ህዳሴ ግድብ ግንባታ ማጠናቀቅና ሌሎች ግዙፍ ፕሮጀክቶችን እውን ማድረግ ላይ ሊያተኩሩ ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያውያን የታላቁን ህዳሴ ግድብ ግንባታ ማጠናቀቅና ሌሎች ግዙፍ ፕሮጀክቶችን እውን ማድረግ ላይ ሊያተኩሩ ይገባል
አዲስ አበባ ግንቦት 18/2015 (ኢዜአ) ኢትዮጵያውያን በዋናነት የታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ በስኬት ማጠናቀቅና ሌሎች ግዙፍ ፕሮጀክቶችን እውን ማድረግ ላይ ሊያተኩሩ ይገባል ሲሉ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የአካባቢና ልማት ጥናት ክፍል ፕሮፌሰር በላይነህ ስማኔ ገለጹ፡፡
የህዳሴ ግድቡን በተመለከተ ህብረተሰቡ ከተለያዩ አቅጣጫዎች የሚመጡ ጫናዎችን በመቋቋምና አቅማቸውን በማስተባበር የግንባታውን ፍጻሜ ማፋጠን አለባቸው ሲሉም ፕሮፌሰር በላይነህ አሳስበዋል፡፡
ኢትዮጵያውያን በዋናነት "የታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ማቀላጠፍና ሌሎች ተያያዥ ግዙፍ ፕሮጀክቶችን እውን ማድረግ ላይ ሊያተኩሩ ይገባል ብለዋል፡፡
ከህዳሴ ግድቡ ባለፈ በቱሪዝም፣ በአሳ እርባታ፣ በትራንስፖርትና በአረንጓዴ ልማት ላይ ትኩረት ሰጥተው መስራት እንደሚገባቸው ፕሮፌሰር በላይነህ ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያ የግድቡ ግንባታ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ በግልጽ እንዳስቀመጠችው የግድቡ መገንባት የመጨረሻው ውጤት የተፋሰሱን አገራት የጋራ ተጠቃሚና አሸናፊ የሚያደርግ ነው ብለዋል፡፡
“እኛ በጋራ ለመስራት ግልጽና ለማንም ያልተደበቀ አቋማችንን አሳይተናል። እነሱ በአባይ ወንዝ ላይ የያዙትን የበላይነት ማጣት አይፈልጉም፡፡ በሌላ መልኩ እኛ የማንቀበለውን የቅኝ ግዛት ዘመን ውል ተግባራዊ ማድረግ ይፈልጋሉ” ሲሉ ገልጸዋል፡፡
የታችኛው የተፋሰሱ ሀገራት ከግድቡ መገንባት በረጅም ጊዜ የሚያገኙትን ጠቀሜታ የሚያውቁት ቢሆንም መቀበል አለመፈለጋቸውንም ፕሮፌሰር በላይነህ ጠቁመዋል፡፡
የህዳሴ ግድቡ መገንባት በታችኛው የተፋሰሱ ሀገራት ህዝቦች የውሃ አጠቃቀምና የኑሮ ሁኔታ ላይ ምንም አይነት ተጽእኖ እንደማያሳድር ፕሮፌሰር በላይነህ በአጽንኦት አስረድተዋል፡፡
ሶስቱ ሀገራት ሁሉንም የጋራ ተጠቃሚና አሸናፊ ሊያደርግ በሚችል አግባብ በጋራ ቢሰሩ መልካም መሆኑን በመጠቆም፤ ኢትዮጵያ ለዚህ ግብ መሳካት ሁሌም ዝግጁ መሆኗን አረጋግጣለች ብለዋል፡፡