ቀጥታ፡

በሀገራችን የሚካሄዱ ግንባታዎች የተፈጥሮ አደጋዎችን መቋቋም የሚችሉ ሆነው ሊገነቡ ይገባል - የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ባለስልጣን

አርባምንጭ  ግንቦት 18/2015 (ኢዜአ) በሀገራችን የሚካሄዱ ግንባታዎች የተፈጥሮ አደጋዎችን በአግባቡ መቋቋም የሚችሉ ሆነው ሊገነቡ እንደሚገባ የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ባለስልጣን አመለከተ ።

በግንባታ ጥራትና ደህንነት ላይ ያተኮረ ሀገር አቀፍ የባለድርሻ አካላት ውይይት በአርባምንጭ ከተማ እየተካሄደ ነው።


 

በፕሮግራሙ ላይ የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር መስፍን ላቀው እንዳሉት በዓለማችን ከተፈጥሮ ፀጋዎች ጋር ተያይዞ ፈተናዎችም መኖራቸውን ጠቅሰዋል።

በተለይም እንደ ርዕደ መሬት ያሉ አደጋዎች ከፍተኛ ጉዳት እያስከተሉ መሆኑን አስታውሰዋል።

የሰው ልጅ ግን የተሰጠውን የተፈጥሮ ፀጋ በአግባቡ በመጠቀም ጉዳቱን ከመቀነስ ባለፈ ትርፋማ ሊሆን ይገባል ብለዋል።

ከእነዚህ አንዱ የግንባታ ስራ መሆኑን አንስተው በሀገራችን የሚካሄዱ ግንባታዎች የተፈጥሮና ሰው ሠራሽ አደጋን መቋቋም የሚችሉ መሆን እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

በቅርቡ በቱርክና ሶሪያ የተከሰተው ርዕደ መሬት ከፍተኛ የሆነ የሰብአዊና ቁሳዊ ኪሣራ ማድረሱን ጠቅሰው ይህ አደጋ ለእኛና ለመላው ዓለም የማንቂያ ደወል ነው ብለዋል።

በኢትዮጵያም የመሬት መንቀጥቀጥ ሁኔታዎች በየጊዜው እንደሚስተዋሉ የጠቀሱት ዳይሬክተሩ፤ በሀገራችን የሚከናወኑ ግንባታዎች የተፈጥሮ አደጋዎችን መቋቋም የሚችሉ ሆነው እንዲገነቡ የዘርፉ አካላት የበኩላቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ጥሪ አቅርበዋል።

ውይይቱ ለሁለት ቀናት የሚካሄድ ሲሆን ከግንባታ ጥራትና ደህንነት ጋር በተያያዘ ጥናታዊ ጽሑፎች ቀርበው ውይይት እንደሚደረግ ይጠበቃል።

ከዚህ ቀደም የተከናወኑ የከተሞች ግንባታ ምን ያህል አደጋን የሚቋቋሙ እንደሆኑ፣ እየተገነቡ ያሉ ግንባታዎች ዘመኑን የሚመጥኑና አደጋን የሚቋቋሙ ናቸው ወይ? በሚሉትና ወደፊት የሚከናወኑ ግንባታዎች መሆን በሚገቡ ጉዳዮች ዙሪያ ሰፊ ውይይት እንደሚደረግም ከመርሃ ግብሩ ለመረዳት ተችሏል።

በውይይቱ ላይ ከ70 በላይ ከተሞች የተውጣጡ የህንፃ ሹሞች፣ የክልሎች ኮንስትራክሽን ቢሮ ሃላፊዎች፣ የኮንስትራክሽን ሙያ ማህበራት ተወካዮች እንዲሁም ሌሎች የፌዴራልና የክልል ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ሃላፊዎችና የጋሞ አባቶች በመሳተፍ ላይ ናቸው።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም